የኢትዮዽያ አየር መንገድ የኮቪድ-19 ክትባቶችን ሊያሰራጭ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮዽያ አየር መንገድ የኮቪድ-19 ክትባቶችን ሊያሰራጭ ነው
ጥቅምት 26/2013 (ኢዜአ) በአፍሪካ ቀዳሚውና በርካታ አለም አቀፍ ሽልማቶችን ያገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነት እና ሎጅስቲክስ አገልግሎት የኮቪድ-19 ክትባቶችን ለአፍሪካና ለመላው አለም ለማሰራጨት መዘጋጀቱን አስታውቋል።
በአመት አንድ ሚሊዮን ቶን የማስተናገድ አቅም ያለው እንዲሁም አስተማማኝ ማቀዝቀዛዎችን በማካተት በአፍሪካ ትልቅና እጅግ ዘመናዊ የጭነት ተርሚናል ባለቤት መሆኑ የተነገረለት አየር መንገዱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ያግዛሉ የተባሉ ቁሳቁሶችን በዓለም ዙሪያ በማዳረስ ወሳኘ ሚና እንደነበረውም ተነግሯል።
የካበተ ልምድና ዕውቅና ያለው አየር መንገዱ የክትባት ቁሳቁሶችን ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ለአለም በማሰራጨት እንደሚደግም የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ተወልደ ገብረማሪያም የተናገሩ ሲሆን አስፈላጊ የተባሉ መድሃኒቶችንና የእለት ደራሽ እርዳታዎችን በማድረስ ከአለም ጤና ድርጅት ከአለም የምግብ ፕሮግራምና ከሌሎች በጎ አድራጊ ድርጅቶች ጋር እየሰሩ መሆኑናቸውን ተናግረዋል።
ስራ አስፈጻሚው ዓለም የወረርሽኙን ክትባት ለማግኘት እየተጠባበቀ ባለበት በዚህ ወቅት ለመላው አለም ለማዳረስ ግንባር ቀደም ሆነው የመስራት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በዚህም የተገነባው ዘመናዊ የጭነት ተርሚናል ጥንቃቄ የሚፈልጉ መድሃኒቶችንና የህክምና ቁሳቁሶችን ለማዳረስ ተመራጭ ስለመሆኑ ኤይር 101 ድረገጽ አስነብቧል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወረርሽኙ በተከሰተበት ወቅት የጭነት አገልግሎት ፍላጎትን ለማሳካት የመንገደኞች አውሮፕላኖችን ወደ ጭነት አውሮፕላኖች ቀይሮ በማሰማራት አስደናቂ ስራዎች ማሳካቱን መረጃው ተጠቁሟል።
የአለም የምግብ ፕሮግራም፣ የአለም ጤና ድርጅት፣ ጃክ ማ ፋውንዴሽን እንዲሁም የቻይና መንግስት እርዳታዎችን ለአምስት አህጉራት በ360 የቻርተር በረራዎች ማዳረሱም መረጃው አስታውሷል።