ቀጥታ፡

ጽንፈኛውን ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማስወገድ ለአንድነታችን ዘብ ልንቆም ይገባል- አቶ ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ ጥቅምት 26/2013 (ኢዜአ) በሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ላይ ጥቃት ያደረሰውን ፅንፈኛውን የህወሐት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማስወገድ ለአንድነታችን ዘብ ልንቆም ይገባል ሲሉ የሲዳማ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ጥቂት የህወሐት ቡድን የሥልጣን ጥማቱን ለማርካት ሀገሪቱን ለማተራመስ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

በቡድኑ የሥልጣን ሱሰኝነት ላለፉት 27 ዓመታት የኢኮኖሚ አሻጥር በመፍጠር የሀገሪቱን ሀብት እንዳሻው ሲዘርፍና ሲበዘብዝ  የነበረ የህዝቦች  ጠላት መሆኑን ገልጸዋል።

የሲዳማ ህዝብም እንደሌሎች ኢትዮጵያዊያን በህወሐት አገዛዝ ጭቆናና አፈና ሲደርስበት መቆየቱን አስታውሰው በለውጡ ኃይል አማካይነት ሲዳማ ህገ-መንግስታዊ መብቱ እንደተከበረለት ጠቁመዋል።

ይህ ቡድን ሀገራዊ ለውጡን በመቀልበስ ዳግም ወደ ሥልጣን ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት እንደማይሳካ ተናግረዋል።

በሀገሪቱ ህዝቦች መካከል መከፋፈልና ጥርጣሬ እንዲፈጠር የተለያዩ ግጭቶችን በመደገስና ንፁሀንን በማስገደል ዳግም ወደ ሥልጣን ለመምጣት ጥረት ሲያደርግ የነበረው የህወሐት ቡድን አሁን ደግሞ የሀገርን ዳር ድንበር እየጠበቀ የሚገኘውን መከላከያ ሰራዊት በማጥቃት ወደ ለየለት ጦርነት ውስጥ ገብቷል ብለዋል።

በግዴለሽነትና ንቀት ጦርነት የጀመረው የወያኔ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማስወገድ ለአንድነታችን ዘብ ልንቆም ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ደጀን ከመሆን ባለፈ መንግስት ለሚያቀርበው ማንኛውም ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

ይህ ቡድን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የሽብር ሙከራዎችን ሊያደርግ ስለሚችል    ሁሉም አካባቢውን በንቃት መጠበቅ እንዳለበትም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

በተለይ ህዝቡ ፀጉረ-ልውጥ ሰዎችና እንግዳ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን በሚመለከትበት ወቅት በአንክሮ መከታተልና ለፀጥታ አካላት መረጃ በማቀበል ትብብር እንዲያደርግም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የክልሉ መንግስት ወደ አካባቢው የሚያስገቡ እቅጣጫዎችን እንዲሁም ጥበቃ የሚያሻቸውን ተቋማት ሁሉ በንቃት እየጠበቀ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም