ኢትዮጵያ ችግሮችን ተቋቁማ በጤናው ዘርፍ ውጤት ማስመዝገቧን የጤና ሚኒስትሯ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ችግሮችን ተቋቁማ በጤናው ዘርፍ ውጤት ማስመዝገቧን የጤና ሚኒስትሯ ገለጹ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ችግሮችን ተቋቁማ በጤናው ዘርፍ ባደረገችው እንቅስቃሴ ውጤት ማስመዝገቧን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናገሩ።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የጤናው ዘርፍ 22ኛ ጉባዔ ላይ ዶክተር ሊያ እንደተናገሩት፤ አገሪቱ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተጽዕኖ ተቋቁማ በዘርፉ ባደረገችው እንቅስቃሴ ካለፉት ዓመታት የተሻለ ውጤት አስመዝግባለች።
ውጤቱ በጤና አገልግሎት ጥራትና ፍትሃዊነት፣ በወረዳ ትራንስፎርሜሽንና ተገልጋይ አክባሪና የጤና ባለሙያዎች በማፍራት ረገድ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
ውጤቱ አገሪቱ በዘርፉ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የሄደችበትን ርቀትና በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ መሆኗን ማሳያ ነውም ብለዋል።
በዓመቱ በዘርፉ 49 ወረዳዎች ሞዴል ያደረጋቸውን ውጤት ያስመዘገቡ ሲሆን፣ 109 ወረዳዎች መካከለኛ አፈጻጸም እንደነበራቸው አስታውቀዋል።
በአገሪቱ ከአራት ዓመታት በፊት በሕይወት ከሚወለዱ አንድ ሺህ ህፃናት መካከል 67ቱ አምስት ዓመት ሳይሞላቸው ይሞቱ የነበረበት ሁኔታ ተለውጦ ምጣኔው ወደ 55 ዝቅ ማለቱን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
በሰለጠነ ባለሙያ የሚሰጥ የወሊድ አገልግሎት ከ28 በመቶ ወደ 50 በመቶ በማደጉ ከሁለት ሚሊዮን በላይ እናቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይ ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ማህበረሰቡን ከድንገተኛ አደጋዎችና ችግሮች መጠበቅ እንዲሁም ማህበረሰቡ በጤና ሥርዓት ላይ ያለውን አመኔታ ለማሳደግ ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
በጉባዔው በጤናው ዘርፍ የተሻለ አፈጻጸም የነበራቸው ተቋማትና ግለሰቦች ተሸልመዋል።
የዓመቱ ልዩ ተሸላሚ የሆኑት የጤና ሚኒስቴርን ለዓመታት በሚኒስትር ዴኤታነት ያገለገሉት ዶክተር ከበደ ወርቁ የጤና ባለሙያዎች የሰውን ልጅን ከሞት ለመታደግ ሙያውን አክባሪና ታማኝ ሆነው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ ባደረጉት እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ መረጃ በመስጠት፣ የወረርሽኙን ተጠቂዎች በማከም ደግሞ ኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ተሸላሚ ሆነዋል።
እንዲሁም 82 ጊዜ ደም የለገሱት አቶ ዳዊት ተስፋዬ ዋንጫና የምስክር ወረቀት ተሸልመዋል።
የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው ባለሙያዎችና ክልሎችም ላበረከቱት አስተዋጽኦ ለሽልማት በቅተዋል።
17Berhanu Tessema and 16 others