ሕወሓት በእኩይ ድርጊቱ እንዳይቀጥል የኢትዮጵያ ሕዝብ ከየትኛውም ጊዜ በላይ አንድነቱን ማጠናከር አለበት ... አቶ ታዬ ደንደአ - ኢዜአ አማርኛ
ሕወሓት በእኩይ ድርጊቱ እንዳይቀጥል የኢትዮጵያ ሕዝብ ከየትኛውም ጊዜ በላይ አንድነቱን ማጠናከር አለበት ... አቶ ታዬ ደንደአ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2013(ኢዜአ) ሕወሓት በእኩይ ድርጊቱ እንዳይቀጥል ሕዝቡ ከየትኛውም ጊዜ በላይ አንድነቱን ማጠናከርና አንዱ ሌላውን መጠበቅ እንዳለበት የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ ተናገሩ።
ኢዜአ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ከአቶ ታዬ ደንደአና ከሕግ ባለሙያው ከአቶ ኤፍሬም ታምራት ጋር ቆይታ አድርጓል።
አቶ ታዬ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) "ከተፈጠረ ጀምሮ በሴራ ውስጥ የቆየ ድርጅት ነው"።
''ድርጅቱ ሲመሰረትም ኢትዮጵያን እስከቻልኩ ድረስ አስተዳድራለሁ፤ ካልሆነ እበትናታለው በሚል መርህ ስልጣን ላይ የቆየ ነው'' ብለዋል።
"በዜጎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን ሲፈጽም፣ ሲያሰቃይና የአገሪቷን ኃብት ሲዘርፍ የኖረ ቡድን ነው" ብለውታል። ።
በትናንትናው እለትም በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት የፈጸመው እንደለመደው ''እሳት ለኩሶ ዳር ቆሞ የሚሆነውን የሚመለከት መስሎት ነው'' ብለዋል አቶ ታዬ።
የሕግ ባለሙያው አቶ ኤፍሬም ታምራትም ሕወሓት ለዓመታት መሰረታዊ የዜጎችን መብት ሲጠስ የቆየ ድርጅት ነው ይላሉ።
አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው መንግስት ከሕገ መንግስት ጀምሮ እስከ አለም አቀፍ ሕግ ድረስ በዚህ ቡድን ላይ እርምጃ መውሰድ የሚያስችለው ሕጋዊነት አለው ብለዋል።
እንደእርሳቸው ገለጻ ከጦርነት አጠቃላይ አውዳሚ ባህሪ አንጻር መንግስት ከፍተኛ ትዕግስት ማሳየቱም የሚደገፍ እንጂ አይነቅፍም።
ድርጅቱ ይህን ሁሉ አልፎ በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በማድረሱ በመንግስት እየተወሰደ ያለው እርምጃ ከሕግም፤ ከሞራልም አንጻር ተገቢ ነው ብለዋል።
አቶ ታዬ በበኩላቸው ሕወሓት ከተመሰረተ ጀምሮ በጥፋት መንገድ የተሰለፈ ቡድን መሆኑን አስታውሰው፤ የተጀመረው እርምጃ መጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል።
በመንግስት በኩል ዜጎችን ከጥቃት መከላከል፣ የዜጎችን ነጻ እንቅስቃሴ ማስጠበቅ እንዲሁም የሕዝብን ደህንነት የመጠበቅ ስራም ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት።
ሆኖም ይህ የጥፋት ቡድን አሁንም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እኩይ ተግባራትን ሊፈጽም ስልሚችል አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ይላሉ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከምንጊዜም በላይ አንድነቱንና ሕብረቱን አስጠብቆ አንዱ የሌላው ጠበቃ መሆን እንዳለበት ጠቅሰዋል።
የሕግ ባለሙያው አቶ ኤፍሬም በበኩላቸው መንግስት በቀጣይ ጥፋተኞችን በሕግ ጥላ ስር የማዋል ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን የአገሪቱን ችግሮች ከምንጩ የማድረቅ ስራና ሕወሓት ውስጥ ያሉ አደገኛ ቡድኖችን ማጥራት ተገቢ
እንደሆነ ምጠቅሰዋል።
የፌዴራል መንግስት ከትናንት ሌሊት ጀምሮ በትግራይ ክልል የሕግ የበላይነት እያስከበረ መሆኑ ይታወቃል።