ቀጥታ፡

ህወሃት መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ለማድረስ መሞከሩ ከባእድ ወራሪ የከፋ የከሃዲነትን ጥግ የሚያሳይ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25/2013 (ኢዜአ) “ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) የትግራይ ህዝብ ደጀን የሆነው የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ለማድረስ መሞከሩ ከባእድ ወራሪ የከፋ የከሃዲነትን ጥግ የሚያሳይ ነው” ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰራዊቱ እየወሰደ ላለው እርምጃ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ጉዳዩን አስመልክቶ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የአገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙሃን ዘጋቢዎች በሰጡት ማብራሪያ ነው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህን ወቅት ህወሃት የመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውሰዋል።

ከዚህ ቀደም ሰራዊቱ ለመደበኛ ተልዕኮ ሲንቀሳቀስ የክልሉ ህዝብ መንገድ በመዝጋትም ጭምር "ጥለህን አትሂድ" እያሉ የሚጠይቁት የህዝብ አለኝታ መሆኑንም ነው ያስታወሱት።

በመሆኑም ለበርካታ ዓመታት ሰላም በማስከበርና በልማት ለትግራይ ህዝብ ደጀን ሆኖ እያገለገለ ባለው ሰራዊት ላይ የተቃጣው ጥቃት ከባእድ ወራሪ የከፋ የከሃዲነትን ጥግ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

“ህገ ወጥ ቡድኑ ኢትዮጵያን በመከፋፈል የሚፈልገውን በሃይል ለመፈጸም የመጨረሻ የክህደት እርምጃ አካሄዷል ነው” ያሉት።

ቡድኑ የትግራይ ልዩ ሃይልን በማንቀሳቀስ በአማራ ህዝብ ላይ ወረራ ለማካሄድ መሞከሩን ጠቅሰው፤ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል።

ህገ ወጥ ቡድኑ የትግራይ ህዝብን እንደ መሸሸጊያ በመጠቀም አገር ሲያተራምስ መቆየቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በመሆኑም የትግራይ ህዝብ ከመንግስት ጎን በመቆም አኩሪ ታሪክ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰራዊቱ እየወሰደ ላለው እርምጃ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ያቀረቡት።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው የተፈጠረው ግጭት በትግራይ ህዝብና በሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝቦች መካከል የተከናወነ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ግጭቱ ከመላው የክልሉ መንግስት መዋቅር ጋር ሳይሆን "ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከሚፈልጉ ከሀዲ ቡድኖች ጋር የተደረገ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

በሂደቱ የትግራይ ህዝብ እንደሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹ ነጻነት እንዲያገኝ እንደሚደረግ በመጠቆም።

መንግስት መረጃዎችን በየጊዜው ለህዝብ ተደራሽ እንደሚያደርግም ተጠቁሟል።

316Muse Mele, Berhanu Tessema and 314 others11 Comments35 SharesLikeCommentShare

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም