ቀጥታ፡

በሩብ ዓመቱ ከማእድን ዘርፍ ከ178 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25/2013 (ኢዜአ) በ2013 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከማእድን ዘርፍ ከ178 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የማእድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ገቢው  ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም ከ170 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብልጫ አስመዝግቧል ብለዋል፡፡

የሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሃብት፣ የመስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተገምግሟል፡፡

በማእድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የማእድን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት በዋነኝነት ከወርቅና ከታንታለም ማዕድናት ገቢ ተገኝቷል፡፡

የወርቅ ወጪ ግብይት ከፍተኛውን የውጭ ምንዛሪ ድርሻ እንደሚይዝም ገልጸዋል፡፡

"የወርቅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭማሪ ማሳየትና የብሔራዊ ባንክ ግብይት ማሻሻያ ባህላዊ አምራቾችን በመሳቡ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧልም" ብለዋል ወይዘሮ ስመኝ፡፡

በተደራጁ የማእድን ኢንተርፕራይዞችና ኩባንዎች ውስጥም ለ28 ሺህ 340 ዜጎች ሥራ መፈጠሩንም አስረድተዋል፡፡

ከተለያዩ ገቢዎችም ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ሚኒስትር ዴኤታዋ አስታውቀዋል፡፡

በክልሎች ለ176 ኢንተርፕራይዞችና ለ198 ከፍተኛ ባለሃብቶች ፈቃድ መሰጠቱም ተገልጿል፡፡

ለአዲስና ነባር የነዳጅ ተቋማት 163 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ካፒታል ሥራ ላይ መዋሉንም ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴሩ የአደረጃጀት፣ የፖሊሲ ዝግጅት፣ የህግ ማእቀፍና የሰው ኃይል ግንባታ ላይ የነበሩ ክፍተቶችን ማሟላቱ  በውጤታማነት የሚጠቀሱ ሥራዎች መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

ዘርፉ የሚመራበት ግልጽ የፖሊሲ ማእቀፋት ዝግጅት ያለመጠናቀቅ፣ከክልሎች ጋር ትስስርና ትብብር ላይ የተመሰረተ ጠንካራ የሥራ ግንኙነት ባለመፈጠሩ ሥራ ያቆሙ ኩባንያዎች ማጋጠማቸውም ተነስቷል፡፡

የረቂቅ ፖሊሲ ዝግጅትና የማእድን አልሚ ተኮር የቁጥጥርና ድጋፍ ሥራዎች ማከናወን፣ የሥነ-ምህዳር መረጃን ማጥራትና ሥራ ያቆሙ ኩባንያዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ጥረት መደረጉ እንደ መፍትሔ የተወሰዱ ተግባራት መሆናቸው ተብራርቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም