ህወሓት የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ለማድረስ መሞከሩ የከሃዲነትን ጥግ ያሳያል ... ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
ህወሓት የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ለማድረስ መሞከሩ የከሃዲነትን ጥግ ያሳያል ... ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2013 (ኢዜአ) “ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የትግራይ ህዝብ ደጀን የሆነው የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ለማድረስ መሞከሩ የከፋ የከሃዲነትን ጥግ የሚያሳይ ነው” ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰራዊቱ እየወሰደ ላለው እርምጃ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል የአማራ ክልል አዋሳኝን አልፎ ጥቃት ለመፈጸም ሞክሮ የነበረ ቢሆንም፤ በአማራ ክልል የጸጥታ ኃይል መክሸፉን ገልጸዋል።
ሰራዊቱ የተቃጣበትን ጥቃት በመመከት ሕግን የማስከበር እርምጃ እየወሰደ መሆኑንም ተናግረዋል።
“ህወሓት የትግራይ ህዝብ ደጀን የሆነው የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ለማድረስ መሞከሩ ከባዕድ ወረራ የከፋ የከሃዲነትን ጥግ የሚያሳይ ነው” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሰራዊቱ በዚህ በሕገ-ወጥ ቡድን ላይ እየወሰደ ባለው እርምጃ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉና ከሰራዊቱ ጎን እንዲቆሙ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ትናንት ከእኩለ ሌሊት በኋላ በሰጡት መግለጫ በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የተሰነዘረው ጥቃት መክሸፉን መግለጻቸው ይታወሳል።