የአገርን ሉዓላዊ ክብር ለማስጠበቅ የቆመን ሠራዊት ማጥቃት አገርን ተኩሶ እንደ መግደል፤ የኢትዮጵያዊያንን ክብር እንደ መንካት ይቆጠራል - ኢዜአ አማርኛ
የአገርን ሉዓላዊ ክብር ለማስጠበቅ የቆመን ሠራዊት ማጥቃት አገርን ተኩሶ እንደ መግደል፤ የኢትዮጵያዊያንን ክብር እንደ መንካት ይቆጠራል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2013(ኢዜአ) የአገርን ሉዓላዊ ክብር ለማስጠበቅ የቆመን ሠራዊት ማጥቃት አገርን ተኩሶ እንደ መግደልና የኢትዮጵያዊያንን ክብር እንደ መንካት ይቆጠራል ሲል መንግስት አስታወቀ።
"የአገር መከላከያ ሠራዊታችን የአገርን ሉዓላዊ ክብር ለማስጠበቅ በተሰማራበት የትግራይ ክልል በጽንፈኛና ከሃዲ ቡድኖች የተሰነዘረበትን ጥቃት በተደራጀ መልኩ በታላቅ አገራዊ ፍቅርና የጀግንነት ስሜት እየመከተ ይገኛል" ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በከሃዲና ፅንፈኛ ቡድን ሴራ ህብረ ብሄራዊ አንድነታችን አይናድም ሲል ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች መልዕክት አስተላልፏል።
በመልዕክቱም "የአገርን ሉአላዊ ክብር ለማስጠበቅ የቆመን ሠራዊት፤ አገር እንጂ ብሄር የሌለውን ሠራዊት፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትክክለኛ ተምሳሌት የሆነን ህብረ ብሄራዊ ሠራዊት፤ ከአገር አልፎ በአለም አቀፍ ሠላም ላይ ዝናና አክብሮትን ያተረፈን ሠራዊት ማጥቃት አገርን ተኩሶ እንደ መግደልና የኢትዮጵያዊያንን ክብር እንደ መንካት ይቆጠራል" ብሏል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል በአገሪቱ እየተካሄደ ባለው ሁለንተናዊ ለውጥ የትግራይን ህዝብ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት በእጅጉ የሚጎዱ ተግባራትን ሲያካሂድ የቆየው "በህወሃት ውስጥ መሽጎ የሚገኝ የማይለወጥና ቆሞ ቀር ቡድን" ራሱን ከለውጡ ጋር በማላመድ የአገሪቷን ትንሳኤ ለማረጋገጥ በሚደረገው የለውጥ ጉዞ የራሱን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ገልጿል።
ይሁንና ይህ አጥፊና ህገ ወጥ ቡድን ከጅምሩ ጀምሮ ለውጡ እንዲደናቀፍ የተለያዩ ሴራዎችን በመሸረብ የሰው ህይወት እንዲጠፋ፤ አካል እንዲጎድል፤ ንብረት እንዲወድምና በሕዝቦች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ሲያደርግ መቆየቱ አይዘነጋም ነው ያለው፡፡
"ይባስ ብሎ የሠራዊታችንን ሠላማዊ እንቅስቃሴ ሲገድብ የቆየው አሸባሪ ቡድን የአገር ምልክትና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተምሳሌት በሆነው በመከላከያ ሠራዊታችን ላይ ጥቃት ከፍቷል" ሲል አስታውቋል፡፡
ጽንፈኛውና ከሃዲው ቡድን አነስተኛ የሰው ሃይል ባለባቸው የሠራዊቱ ካምፖች ድንገተኝነትን ተጠቅሞ ጥቃት መፈፀሙን ገልፇል።
ጀግናው ሰራዊት "ወትሮም ዋጋ ከፍሎ አገርን ማዳን ልምዱ ነውና የተቃጣበትን ጥቃት ለመመከት ፅንፈኞችን በመፋለም ላይ ነው" ይላል የመንግስት መግለጫ፡፡
በአገር ንብረት ዘረፋ፣ በግድያ፣ በአካል ማጉደልና በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚታወቀው ከሃዲውና ጽንፈኛው ቡድን "በአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የሠራዊታችንንና የሌሎች ሃገራትን ዩኒፎርም አስቀድሞ አመሳስሎ በማምረትና የራሱን ሃይል በማልበስ ገድለናል፣ ማርከናል የሚል የተለመደ ማደናገሪያውን የክልሉን ሚዲያ ተጠቅሞ በመንዛት ላይ እንደሚገኝም ጠቁሟል፡፡
እውነታው ግን "ጀግናው ሠራዊታችን በታላቅ ጀግንነት፣ በፍፁም የአገር ፍቅር ስሜትና በአንድነት መንፈስ የፅንፈኛውና የከሃዲውን ጥቃት መመከቱ ነው" ብሏል፡፡
"እኔ ከሌለሁ ኢትዮጵያ ትፍረስ" የሚለው የስልጣን ጥመኛው ቡድን ያሰባሰበው የልዩ ሃይልና ሚሊሻ በአንዳንድ አካባቢዎች የመዋጋት ፍላጎት እንደሌለውና መንግስት ዋስትና እንዲሰጠው እንደሚፈልግም ገልጿል።
"ተገዳችሁና ሳትፈልጉ ወደ ጦርነት የገባችሁ የትግራይ ክልል ልዩ ሃይል አባላት! በሠላማዊ መንገድ ወደ አጎራባች ክልሎችና በአቅራቢያችሁ ወዳለው የመከላከያ ሠራዊት ከገባችሁ መንግስት ሙሉና አስተማማኝ ዋስትና እንደሚሰጣችሁ ያረጋግጥላችyል" ሲል አስታውቋል፡፡
መንግስት ለትግራይ ሕዝብ ባስተላለፈው መልዕክትም
"ሠላማችሁን ለማስጠበቅ ከሃያ ዓመታት በላይ ከጎናችሁ ተሰልፎ የተዋደቀውን የአገር መከላከያ ሠራዊት፤ ችግራችሁን እየተካፈለና ልማታችሁን እየደገፈ አብሯችሁ በመልካም ወንድማማችነት የኖረውን ይህንን ጀግና ሠራዊት መውጋት ታሪክ ይቅር የማይለው የትግራይን ህዝብ የማይመጥን ከመሆኑ ባሻገር በዓለም ታሪክ አንድ መደበኛ ጦር በደባና በአሻጥር በገዛ ወገኑ ተወግቶ የማያውቅ መሆኑን ተረድታችሁ በዚህ አሳፋሪ ድርጊት ባለመሳተፍና ከሠራዊታችን ጎን በመሰለፍ የተለመደ ጀግንነትና ቁርጠኝነታችሁን እንድታረጋግጡ ጥሪ እናቀርብላችyለን" ብሏል፡፡
ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦችም "የአገር መከላከያ ሠራዊት ትናንት ከላብ ጠብታ እስከ ህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ዛሬም በገንዘቡና በጉልበቱ መላ ሕዝቡን እየደገፈ የመጣ ምስጋና እንጂ ጥቃት የማይገባው የሕዝብ ልጅ መሆኑን አስታውሳችሁ ይህንን ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት እንድታወግዙትና የአገራችንን ሕብረ ብሄራዊ አንድነት ለማስከበርና አጠናክሮ ለማስቀጠል በምንወስደው እርምጃ ከጎናችን እንድትሆኑ ጥሪያችንን እናቀርባለን" ነው ያለው፡፡