ምርምሮች የጎንዮሽ ጉዳት እንዳያስከትሉ የሚያስችል የሥነ-ምግባር መመሪያ ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው

71

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25/2013 (ኢዜአ) በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚደረጉ ምርምሮች የጎንዮሽ ጉዳት እንዳያስከትሉ የሚያስችል የሥነ-ምግባር መመሪያ ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በመመሪያው ዝግጅት ላይ ያተኮረ ዐውደ ጥናት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በሚኒስቴሩ የምርምር ሥነ ምግባር ዳይሬክተር ዶክተር ዳንኤል ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት መመሪያው እየተዘጋጀ ያለው ምርምሮች በሚካሄዱበት ወቅት የጎንዮሽ ጉዳት እንዳይኖራቸው ታስቦ ነው።

ምርምሮች የሥነ-ምግባር መመሪያን ተከትለው ሲካሄዱ የህብረተሰቡን ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጡ አመልክተው፤ ምርምሮችን ደንቡን በተከተለ መልኩ ለማካሄድ መመሪያው ማስፈለጉን አስረድተዋል።

መመሪያው በሰው፣ በእጽዋት፣ በእንስሳት፣ በምህንድስናና በአካባቢ ጉዳዮች ዙሪያ ለሚሰሩ ምርምሮች  ትኩረት መስጠቱንም ተናግረዋል።

ምርምሮች በአካባቢ ላይ ሲሰሩ ብክለትን በማያስከትል ሁኔታ ለማካሄድ ያስችላል ብለዋል ዳይሬክተሩ ።

ለአንድ ዓመት ሲዘጋጅ በቆየው መመሪያ ዝግጅት ላይ 13 ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ተሳትፈዋል።

በመመሪያው ላይ ግብዓቶች ከተሰበሰቡ በኋላ ታትሞ ለዩኒቨርሲቲዎችና ለምርምር ተቋማት እንዲሁም ለህብረተሰቡ እንደሚሰራጭ ዶክተር ዳንኤል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም