ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ አዋሬ ገበያ በደረሰ የእሣት አደጋ አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወደመ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በተለምዶ አዋሬ ገበያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በደረሰ የእሣት አደጋ አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል። 

የከተማ አስተዳደሩ የእሣትና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት መሪ አቶ ጉልላት ጌታነህ የእሣት አደጋው ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ከሌሊቱ 10 ሠዓት ከ54 አካባቢ መድረሱን ገልጸዋል።

አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ሲወድም በተደረገው ርብርብ 10 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ማዳን መቻሉን እንዲሁም በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ተናግረዋል።

አደጋው የደረሰበት አዋሬ ገበያ የሚገኙ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች በጣም የተጠጋጉና የተገነቡባቸው ቁሳቁስም ተቀጣጣይነት ያላቸው መሆናቸው እሣቱ በፍጥነት እንዲዛመት አድርጓል ብለዋል።

እሣቱን ለመቆጣጠር 1 ሠዓት ከ50 ደቂቃ የፈጀ ሲሆን፤ 22 ተሽከርካሪዎችና 80 የእሣትና ድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች ተሰማርተዋል፤ 130 ሺህ ሊትር ውሃም ጥቅም ላይ ውሏል።

የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች አባላትና የአካባቢው ማኅበረሰብም እሣቱን ለማጥፋት ርብርብ አድርገዋል።

የአደጋው መንስኤና በምን ያህል ሱቆች ላይ አደጋ ደረሰ የሚለው እየተጣራ መሆኑንም አቶ ጉልላት ተናግረዋል።

በተለምዶ አዋሬ ገበያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በ2004 ዓ.ም ተመሳሳይ የእሣት አደጋ ደርሶ እንደነበር አስታውሰዋል።

በኮሚሽኑ በተደረገ ጥናት የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በተለምዶ አዋሬ ገበያ በክፍለ ከተማው ከሚገኙ ወረዳዎች ለአደጋ ከፍተኛ ተጋላጭ እንደሆነ መለየቱንም ነው አቶ ጉልላት የጠቆሙት።

ቀደም ሲልም የኮሚሽኑ የስራ ሃላፊዎች ከአዋሬ ገበያ አካባቢና ከወረዳው ማኅበረሰብ ጋር በመወያየት በአካባቢው የሚገኙ ሰዎች እንዲነሱና ወደ ሌላ ቦታ እንዲሄዱ ምክረ ሀሳብ መቅረቡንም አንስተዋል።

የቀረበውን ምክረ ሀሳብ ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ የየካ ክፍለ ከተማና የወረዳው አመራሮች የትኩረት ማነስና የማስፈጸም ድክመት መኖሩንም አመልክተዋል።

በመዲናዋ ለእሣትና ድንገተኛ አደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ለሚኖሩ ነዋሪዎች አስቸኳይ መፍትሔ የሚሆነው ከቦታዎቹ ማንሳት እንደሆነም ተናግረዋል።

ዘላቂው መፍትሔ ደግሞ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን መልሶ በማልማትና በማዘመን ተጋላጭነታቸውን መቀነስ መሆኑን ነው አቶ ጉልላት ያብራሩት።

በነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች መፍትሔ እስኪበጅላቸው ድረስ የአደጋ ቅደመ-ጥንቃቄ መልዕክቶችን ተግባራዊ ማድረግና አደጋ ሊፈጥሩ የሚችሉ ተቀጣጣይ ነገሮችን አለመጠቀም መሆኑንም አሳስበዋል።

የእሣትና ድንገተኛ አደጋ ሲያጋጥም በነጻ የስልክ መስመር 939፤ በቀጥታ የስልክ መስመሮች 011 155 53 00 ወይም በ011 156 86 01 ደውሎ ማሳወቅ ይቻላል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሣትና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ስጋት ብሎ በለየው  የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ በተለምዶ አየር አምባ በሚባለው አካባቢ መስከረም 29 ቀን 2013 ዓ.ም በደረሰ የእሳት አደጋ የአራት ሕፃናት ሕይወት ማለፉ የሚታወስ ነው።

በአደጋው አንድ ሰው የቆሰለ ሲሆን በስድስት ሱቆችና በመኖሪያ ቤቶች ላይ በደረሰው ቃጠሎ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረትም ወድሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም