ቀጥታ፡

የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ የሚወሰዱ ማናቸውንም እርምጃዎች እንደሚደግፍ የሐረሪ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ

ሐረር፣ ጥቅምት 25/2013 (ኢዜአ) የዜጎችን ደህንነትና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚወሰዱ ማናቸውንም እርምጃዎች እንደሚደግፍ የሐረሪ ክልላዊ መንግስት ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

የክልሉ መንግስት በመግለጫው እንዳመለከተው መከላከያ ሠራዊቱ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነት ለማስከበር፣ ሰላምና ደህንነታቸውን ለመጠበቅ የገነቡት ጠንካራ፣ ብሔራዊና ሀገራዊ ተቋም ለመሆኑ በተግባሩ ደጋግሞ አረጋግጧል።

ሕገመንግሥቱንና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን መሠረት አድርጎ የተሰጠውን ተልዕኮ በላቀ ወታደራዊ ዲስፕሊንና ብቃት በመወጣት ከራሱ አገርና ህዝብ አልፎ የሌለውን ሀገር የሰላም በማስከበር ታላቅ ከበሬታ፣ አመኔታና ይሁንታ ያተረፈ ተቋምና ሰራዊት እንደሆነ ተገልጿል።

ሰላምና ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ሌት ተቀን ዘብ በቆመበትና ከመቼውም ጊዜ በላይ አገራዊ አንድነትና ሰላም በሚያስፈልግበት በአሁኑ ወቅት ተስፋ የቆረጠው የህወሓት የጥፋት ቡድን ትግራይ በሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ካምፕ ላይ  የሞከረው ጥቃት  በመላው የኢትዮጵያ ህዝብና በሉዓላዊነታችን ላይ የተፈጸመ አሳፋሪ ተግባር ተደርጎ የሚወሰድ ነው ብሏል። 


እንደ ቁማር ማስያዣ ሲጠቀምበት ከኖረው ሰላም፣ እኩልነትና አንድነት ወዳዱ የትግራይ ህዝብ መሃል የመሸገው የህወሓት የጥፋት ቡድንን ከነተላላኪዎቹ ለይቶ ለማጽዳት መንግስትና ሰራዊቱ የሚወስዱትን ማናቸውንም እርምጃዎች የሐረሪ ክልላዊ መንግስት  እንደሚደግፍ  በመግለጫው  አስታውቀዋል።

መላው የክልላችን ህዝብ ከምንጊዜውም በላይ የአካባቢውን ሰላምና ጸጥታ በከፍተኛ ትኩረትና ንቃት ከመጠበቅ ባሻገር በመንግስትና በሚመለከታቸው አካላት የሚሰጡትን መግለጫዎች በትኩረት እንዲከታተል ጥሪ ያቀርቧል ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም