የትግራይ ሕዝብ መንግስት በሚወሰደው እርምጃ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን ሊቆም ይገባል- ኢዜማ - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ሕዝብ መንግስት በሚወሰደው እርምጃ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን ሊቆም ይገባል- ኢዜማ
የትግራይ ሕዝብ መንግስት የሚወሰደው እርምጃ ለሀገር አንድነት እና ሰላም ማስከበር ብቻ እንደሆነ በመረዳት ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን ሊቆም እንደሚገባ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ገለጸ።
ሕወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው የኢፌዴሪ መከላለከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመውን ድርጊትም አውግዟል።
ኢዜማ በማህበራዊ ድህረ ገጹ እንዳስታወቀው በአሁኑ ወቅት ሕወሓት በተለየ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ምልክት የሆነው መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመው ድርጊት በፍፁም በዝምታ የሚታለፍ አይደለም።
ሕወሓት በተለያዩ ጊዜያት የሥርዓት አልበኝነት ጥሪዎችን ሲያስተላልፍ መቆየቱንና በክልሉ ሕግን ተላልፎ የተለዩ ድርጊቶችን ሲፈጽም እንደነበር አመልክቷል።
ከዚህ በፊት የነበረው ችግር በንግግር መፈታት ከሚችልበት ምዕራፍ አልፎ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ በመገኘቱ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሀገር አንድነት እና ሰላምን ለማስከበር የሚወስዳቸውን እርምጃዎች በመደገፍ የኢዜማ አባላት እና አመራር ከጎኑ እንደምንሰለፍ እናሳውቃለን ብሏል።
በመንግስት በሚወስዳቸው እርምጃዎች ሰላማዊ ዜጎችን ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስባቸው አስፈላጊው ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም አመልክቷል።
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ይህንኑ በመረዳት አብሮነታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ፤ ለሰላም እና ደህንነት እንቅፋት የሚሆኑ ማንኛውንም እንቅስቃሴዎች ከማድረግ ተቆጥቦ፤ አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ብሏል ኢዜማ በመግለጫው።