ቀጥታ፡

በማእከላዊ ጎንደር ዞን አምስት ብሬል መትረየስ መሳሪያ በቁጥጥር ስር ዋለ

ጎንደር፣ ጥቅምት 25/2013( ኢዜአ) ለጥፋት ተልእኮ ማስፈጸሚያነት በድበቅ ሲጓጓዝ የነበረ አምስት የብሬል መትረየስ በቁጥጥር ስር መዋሉን የማእከላዊ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የኮሚኒኬሽንና ሚዲያ ዋና ክፍል ሃላፊ ኮማንደር ውብነህ አስናቀው ለኢዜአ እንደተናገሩት መሳሪያዎቹ የተያዙት ትናንት ማምሻውን በዞኑ አለፋ ወረዳ ፍንጅት በተባለው የጥበቃ ኬላ ፈታሾች ባደረጉት ጥብቅ ክትትል ነው።

የጦር መሳሪያዎቹ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 2- 55523 አዲስ አበባ በሆነ ቶዮታ ፒካፕ መኪና በድብቅ ተጭኖ በአለፋ በኩል ወደ ባሕርዳር ሊገባ የነበረ መሆኑ ተመልክቷል።

የጦር መሳሪያዎቹን በድብቅ ጭኖ ሲያጓጉዝ ነበር የተባለ አንድ ተጠርጣሪ ግለሰብም በቁጥጥር ስር ውሎ በፖሊስ ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑንም ኮማንደሩ አስታውቀዋል። 

የክልሉን ሰላም የማይሹ ሃይሎች የጥፋት ተልዕኳቸውን ለማስፈጸም በየጊዜው በርካታ የጦር መሳሪያዎችን ወደ ክልሉ ለማስገባት ሙከራ እያደረጉ መሆናቸውን አውስተዋል።

በዞኑም ሆነ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ያለው ህዝብ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት ለፖሊስ እንዲጠቁም አሳስበዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም