ሕወሐት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል--ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ - ኢዜአ አማርኛ
ሕወሐት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል--ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ
አዲስ አበባ ጥቅምት 24 /2013 (ኢዜአ) በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ሕወሐት ጥቃት ጥቃት ማድረሱን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በፌስ ቡክ ገፃቸዉ ላይ ባሰፈሩት መረጃ ገልፀዋል ።
ሰሜን ዕዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርጓል። ይህ ሠራዊት ከሃያ ዓመታት በላይ የትግራይን ሕዝብ ሲጠብቅ የቆየ ሠራዊት ነው።
በቦታው የሚገኘውም የትግራይን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል ነው። ሕወሐት ግን እንደ ባዕድና እንደ ወራሪ ሀገር ሠራዊት ቆጥሮ፤ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመምታትና ለመዝረፍ ተነሥቷል ።
በዳልሻሕ በኩልም ጦርነት ከፍቷል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ።
መንግሥት የትግራይ ሕዝብ እንዳይጎዳ በማሰብ፣ ጦርነት እንዳይፈጠር የትእግሥቱ ጫፍ ድረስ ታግሷልያሉት ዶክተር አብይ ጦርነት የሚቀረው ግን በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ እንዳልሆነም ጠቁመዋል።
የመከላከያ ሠራዊታችን በኮማንድ ፖስት እየተመራ ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል። ቀዩ መሥመር የመጨረሻው ነጥብ ታልፏል። ሀገርና ሕዝብ ለማዳን ሲባል ኃይል የመጨረሻው አማራጭ ሆኗልም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነገሮችን በሰከነ መንፈስ እንዲከታተል፣ በየአካባቢው ሊከሠቱ የሚችሉ ትንኮሳዎች በንቃት እንዲቃኝና ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን እንዲቆም ጥሪ አቀርበዋል።