በንጹሃን ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጭፍጨፋ ሁሉም አካል ሊያወግዘው ይገባል... የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ - ኢዜአ አማርኛ
በንጹሃን ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጭፍጨፋ ሁሉም አካል ሊያወግዘው ይገባል... የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ
ባህርዳር፤ ጥቅምት 24/2013 (ኢዜአ) በንጹሃን ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጭፍጨፋ ሰብአዊነት የሚሰማው ሁሉም አካል ሊያወግዘው እንደሚገባ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ።
የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በተጠናቀቀው የመጀመሪያ ሩብ በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸምና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በባህርዳር ከተማ እየተወያዩ ነው።
በፓርቲው የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ አቶ አብርሃም አለኸኝ ውይይቱን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት በየጊዜው የሚፈጸሙ ጭፍጨፋና ግፍ መረጃውን ለመደበቅ ከመሞከር ወጥቶ በይፋ በመናገር ቁርጠኛ ትግል ማካሄድ ወቅቱ የሚጠይቀው አካሄድ ነው።
አንዳንድ አካላት የዜጎች መጨፍጨፍ፣ መሰደድ፣ ንብረት መውደምና መገፋትን በመደበቅ ሀገራዊ አንድነትንና ለውጡን ማስቀጠል የሚቻል የሚመስላቸው አሉ ብለዋል።
በትህነግና ኦነግ ሸኔ ትስስር ንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸው መጨፍጨፍ አሁን መግታት ካልተቻለ አደጋው ለሁሉም የሚተርፍ መሆኑንም ገልጸዋል።
በምዕራብ ወለጋ ዞን በጉሊሶ ወረዳ ንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸው የተፈጸመባቸው ጥቃት የኢትዮጵያ ብሔርሰቦች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና ሌሎች አካላት በማውገዝ አጋርነታቸውን ሊያሳዩ ይገባል ብለዋል።
በሀገሪቱ በአማራና ኦሮሞ ወጣቶችና ህዝብ ጠንካራ ትግል አምባገነኑ የትህነግ ቡድን ከመንበረ ስልጣኑ በመገፋት ጠርዝ ላይ ሆኖ በግጭት ለማትረፍ እየሰራ እንደሚገኝ አውስተዋል።
አምባገነኑን ቡድን በማስወገድ ለውጡን ማምጣት ቢቻልም ላለፉት 40 ዓመታት የተዘራው የተሳሳተ ትርክት በተለያየ አቅጣጫ ንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸው ለጥቃትና እልቂት እየዳረገ ይገኛል ብለዋል።
እንደ ሀላፊው ገለጻ ንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸው በመጨፍጨፍ የሚካሄድ የፖለቲካ ንግድና ትርፍ በአፋጣኝ በማስቆም የኢትዮጵያን አንድነትና የለውጡን ቀጣይነት ማረጋገጥ ይገባል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲና ህዝቡ ለውጡን በማስቀጠል ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች በእኩል መብታቸው ተከብሮ የሚኖሩባት ሀገር ለመገንባት ቁርጠኛ ሆነው የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አቶ አብርሃም ተናግረዋል።
ይህም የሚሳካው መላው ኢትዮጵያዊያን ንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸው ከሚፈጸምባቸው ጭፍጨፋና እልቂት በጋራ መታገል ሲቻል መሆኑን በመገንዘብ በአንድነት ሊቆሙ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለስብሰባ ተብለው የተጠሩ ንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸው በግፍ የተፈጸመባቸው ጥቃትና ጭፍጨፋ በአደባባይ ወጥቶ ካለማውገዝ በላይ ትልቅ በደል የለም ብለዋል።
"ዛሬ ላይ እየተፈጸመ ያለውን አሰቃቂ ክስተት የሚያስተምረን ነገር ቢኖር በዓለም ታሪክ ሁል ጊዜም አሸናፊዎች ግፍ የተፈጸመባቸው መሆኑን ተገንዝበን በጋራ መስራት ይኖርብናል" ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የፓርቲው ውይይት በዋናነት የሚያተኩረው እየደረሱ ያሉ ጭፍጨፋዎችን ለማስቆም በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ዙሪያ ለመምከር መሆኑን አስታውቀዋል።
በባህርዳር ከተማ ዛሬ የተጀመረው የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ውይይትም ለአራት ቀናት የሚቆይ መሆኑን ከወጣው መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል።