ቀጥታ፡

የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ ኮቪድ-19 ላይ ማህበረሰቡ ለውጥ እንዲያመጣ መሆን እንዳለበት ተጠቆመ

አዲስ አበባ ጥቅምት 24/2013 (ኢዜአ) የመገናኛ ብዙሃን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የዘገባ ይዘት ማህበረሰብ የባህሪይ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል መሆን እንዳለበት ተገለጸ።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲና የአሜሪካው ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የኮሙዩኒኬሽን ፕሮግራም ማዕከል የኢትዮጵያ ቢሮ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አዘጋገብ አስመልክቶ ለኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በጋራ ያዘጋጁት የበይነ መረብ ስልጠና ዛሬ ተጀምሯል።

የስልጠናው አላማ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አስመልክቶ ለማህበረሰቡ ትክክለኛ፣እውነተኛና ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን የሚሰጡበትን ክህሎት ማዳበር እንደሆነ ተገልጿል።

የዛሬው የስልጠና መክፈቻ ወረርሽኙን አስመልክቶ መገናኛ ብዙሃን እንዴት በሃላፊነትና በጥንቃቄ መዘገብ አለባቸው? በሚለው ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው።

የዓለም የመገናኛ ብዙሃን መምህርና አሰልጣኝ ፕሮፌሰር ቶማስ ላንስነር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን አስመልክቶ ከተለያዩ አካላት ብዙ መረጃዎች እየወጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን አስመልክቶ ማህበረሰቡን በቁጥራዊ መረጃዎች ከማሰልቸት ይልቅ እውነተኛ የሰዎችን ታሪኮች በማቅረብ የባህሪይ ለውጥ እንዲመጣ መስራት አለባቸው ብለዋል።

ማወቅ ባህሪን ይቀይራል ይህም ሰዎች ተግባራዊ ለውጥ እንዲያመጡ ያደርጋቸዋል ያሉት ፕሮፌሰር ቶማስ መገናኛ ብዙሃንም ይሄንኑ መንገድ ተከትለው መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የሚኖሩበትን ማህበረሰብ ባህል፣ የስነ ልቦና ውቃሬና የእድሜ ደረጃ ጠንቅቀው ሊያውቁ  እንደሚገባም አመልክተዋል።

የዘገባዎች አቀራርብ ሳቢና ሰዎች ልብ ውስጥ እንዲቀሩ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መረጃዎችን ቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ ለማህበረሰቡ ማቅረብ እንደሚገባ በመጠቆም።

መገናኛ ብዙሃን የባህሪይ ለውጥ ለማምጣት የማህበረሰብ መሪዎች፣ ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የባህል መሪዎችን መጠቀም እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ሙዚቃዎች፣ የስነ ጥበብ ስራዎችና ባህልን ተጠቅሞ መልዕክቶችን ማስተላለፍ እንደሚቻልና ይሄም የባህሪይ ለውጥ ለማምጣት አስተዋጽኦ እንዳለው ነው ፕሮፌሰር ቶማስ ያብራሩት።

ሰዎች በተሳሳተ እምነትና አመለካከት የማይሆኑ ውሳኔዎችን እንዳይወስኑ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ትክክለኛና እውነተኛ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃን ገለልተኛ በሆነ መልኩ ተአማኒነት ያላቸውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መረጃዎችን ካቀረቡ በማህበረሰብ ውስጥ ያላቸውን እምነት መገንባትና ተቀባይነታቸውን ማሳደግ እንደሚችሉም ተናግረዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጨምሮ ሌሎች ቀውሶች በሚኖሩበት ወቅት መገናኛ ብዙሃን "ምንም አይነት ጉዳት አለማድረስ" የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ በመከተል ሰዎችን ሊጎዱ የሚችሉ መረጃዎችን ማቅረብ እንደማይገባቸው አመልክተዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ወረርሽኙን አስመልክቶ "እሱ እንዳለው እሷ እንዳላችው" የሚለውን መረጃ ተቀብሎ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን መንገድ ተጠቅመው የመረጃውን ትክክለኛነት ማረጋጋጥ እንደሚገባቸው ነው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያው የጠቆሙት።

መንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየሰሩት ያለው ስራ በቅርበት በመከታታል ተጠያቂነትንና ግልጽነትን ሊያስፍኑ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ኮቪድ-19 ወረርሽኝ አስመልክቶ የሚያቀርቧቸውን መረጃዎች ከትክክለኛና ተአዓማኒነት ካላቸው ምንጮች መውሰድ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

ሰዎች በሕይወታቸው ትክክለኛ ውሳኔዎችን እንዲወስኑ ተገቢውን መረጃ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለለፉ መረጃዎችን ሴቶች፣ ህጻናትና አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ያማከሉ ሊሆኑ ይገባልም ብለዋል።

የጋዜጠኞች ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከፍተኛ ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸውናገልጸው ጋዜጠኞች አስገላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ስራቸውን ማከናወን እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ዛሬ የተጀመረው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አዘጋገብ ስልጠና በየሶስት ቀናቱ የሚካሄድ ሲሆን ጥቅምት 27 እና 30 ቀን 2013 ዓ.ም የመገናኛ ብዙሃን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መረጃዎችና ማህበረሰባዊ ለውጥ እንዲሁም ሁሉንም ተደራሽ ያደረገ መረጃ አሰጣጥን የሚዳሰሱ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም