በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት ሰብአዊነት የሌለው አረመኔያዊ ድርጊት ነው... ዶ/ር አረጋዊ በርሄ - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት ሰብአዊነት የሌለው አረመኔያዊ ድርጊት ነው... ዶ/ር አረጋዊ በርሄ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2013 (ኢዜአ) በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በዜጎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት አረመኔያዊ ድርጊት መሆኑን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ተናገሩ ።
ሊቀመንበሩ እንደገለፁት ድርጊቱ ፍጹም ሰብአዊነት የጎደለውና አረመኔያዊ ድርጊት ሽብርን እንደ አላማ አድርገው የያዙ ሰዎች የሚያካሂዱት እኩይ ተግባር ነው ብለዋል።
የሽብር ተግባሩ በተቀናጀ መልኩ ለውጡን የማይፈልጉ ጸረ-ሰላም ሃይሎች የፈጸሙትና ሆን ተብሎ በህዝቦች መካከል ትርምስ ለመፍጠር የተደረገ ነው ብለዋል።
ድርጊቱ በአገር ደረጃ የተያዙ ትላልቅ የልማትና የእድገት ስራዎችን ለማደናቀፍ አልሞ የተፈፀመ መሆኑንም ተናግረዋል።
ይህንንም በመገንዘብ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ተባብሮ እና አንድነቱን አጠናክሮ ሊቃወመው ይገባል ብለዋል።
ይህ አይነቱን ወደ ትርምስ፣ እልቂትና መነጣጠል የሚያመራ ድርጊት በተባበረ ክንድ መመከት ይገባልም ነው ያሉት።
መንግስት ተቀዳሚ ስራው የህዝቦችን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ነው ያሉት ዶክተር አረጋዊ፤ በዚህ ላይ ተግቶ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በዚህ ክፉ ድርጊት ላይ የተሰማሩ ሃይሎችንም ጠንካራ እርምጃ በመውሰድ ህግ የማስከበር ስራውን ማጠናከር እንደሚገባ ገልዋል።
የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበረሰቡ እና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ለሰላም ዘብ መቆም አለባቸው ብለዋል።
በጥቃቱ እስካሁን 34 ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ ከ50 እስከ 60 የሚደርሱ የአርሶ አደር መኖሪያ ቤቶችና አንድ ትምህርት ቤት መቃጠሉን ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።