የዜጎች በህይወት የመኖር መብት አለመከበር በእጂጉ እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የዜጎች በህይወት የመኖር መብት አለመከበር በእጂጉ እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ገለጸ
አዲስ አበባ ጥቅምት 24/2013 (ኢዜአ) የዜጎች በህይወት የመኖር መብት አለመከበር በእጂጉ እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ገለጸ።
ተቋሙ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው የዜጎች በህይወት የመኖር መብት አለመረጋገጥና አደጋ ላይ መውደቁ በእጂጉ አሳስቦኛል ብሏል።
በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ሲደርሱ የነበሩ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግድያዎች፣መፈናቀሎችና ዘርፈ ብዙ ጥቃቶች በማስረጃ ተመስርቶ ለሚመለከተው የመንግሥስት አካል ምክረ ሀሳቦች ሲያቀርብ መቆየቱን አስታውሷል።
''ይሁን እንጂ ችግሩ ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰ ወደ ጅምላ ግድያ በመሸጋገር ላይ ይገኛል'' ብሏል በመግለጫው።
በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ማንነትን መሰረት አድርጎ በተፈፀመው ጥቃት በእጂጉ ማዘኑን ገልጾ መጭው ሁኔታና አዝማሚያም ያሳስበናል ሲል ገልጿል።
መንግሥት የሰዎችን በህይወት የመኖር መብት ለማረጋገጥ እየሄደበት ያለበት መንገድ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል ያለው መግለጫው ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ ለከፋ ችግር ይዳርጋል ሲል ስጋቱን አስቀምጥል።
የሚያሰጋ ሁኔታ ውስጥ እንደምንገባ የሚያመላክት ነው በማለት ነው እንባ ጠባቂ ተቋሙ ያስገነዘበው።
በመሆኑም የፌዴራል መንግሥትና የሁሉም ክልል መንግሥታት የጸጥታና የድህንነት መዋቅር በቅንጅት በመስራት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የዜጎችንም ሰላም እንዲጠብቁ ጠይቋል።
በመጨረሻም ለሟች ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝቷል።