የሃይማኖት ተቋማት ለሰላም መስፈን የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖት ተቋማት ለሰላም መስፈን የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ ጥቅምት 24/2013 (ኢዜአ) ሰላም በግለሰብ፣ በማህበረሰብና በአገር አቀፍ ደራጃ እንዲሰፍን የሃይማኖት ተቋማት የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ።
"ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን የአብሮነታችን እና የሰላማችን ዋስትናዎች ናቸው” በሚል መሪ ቃል የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።
የሰላም ሚኒስቴር ከጉባኤው ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በእዚህ መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኃይላይ ብርሃነ፣ የሃይማኖት ተቋማት የህዝቡን አብሮ የመኖር ባህል በማጠናከር በኩል ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
የምክክር መድረኩ ዋና ዓላማም ለዘመናት የቆየውን በሰላም አብሮ የመኖርና የመከባበር እሴት ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል የሃይማኖትና የእምነት ተቋማት በሚጫወቱት ሚና ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች እንዲሁም የተለያዩየ ሃይማኖትና እምነት ተከታዮች አገር መሆኗን አስታውሰው፣ የሃይማኖት ተቋማት የህዝቦችን በሰላም አብሮ የመኖር እሴት ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ በኩል ሚናቸው የማይተካ መሆኑን ገልጸዋል።
ቤተ እምነቶች ከሰላም ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያላቸው በመሆኑ የእያንዳንዱ ሃይማኖት መሪዎችና አባቶች በሃይማኖታዊ አስተምህሮት ለሰለም ቀጣይነት ባለው መልኩ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባም አቶ ኃይላይ አስገንዝበዋል።
የሁሉም ነገር መነሻና መድረሻ ሰላም በመሆኑ ሰላም በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲሰፍን የሃይማኖት ተቋማቱ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ በበኩላቸው ጉባኤው በኢትዮጵያ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እውን ለማድረግና በአባል የሃይማኖት ተቋማት ሙሉ ይሁንታ መመስረቱን አስታውሰዋል።
"ጉባኤው ተመስርቶ ሥራ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን፣ በህዝቦች መካከል አብሮነትን ለማጠናከርና አገራዊ መግባባትን ለማስፈን የሚያችሉ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ነው" ብለዋል።
ሃይማኖትና ብሔርን ሽፋን በማድረግ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ለዘመናት በሰላምና በመከባበር የኖረውን ሕዝብ እያወኩና አለመተማመን እየፈጠሩ በመሆኑ ጉባኤው ድርጊታቸውን እንደሚያወግዝ ተናግረዋል።
የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ ምዕመናን ራሳቸውን የፀረ ሰላም ኃይሎችን አስተሳሰብ በሚያራምዱ አካላት ሰለባ እንዳይሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባላት እና በክልል ያሉ የሃይማኖት ተቋማት አባቶች የተገኙ ሲሆን የምክክር መድረኩ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይም ታውቋል።