ቀጥታ፡

የላልይበላ ውቅር አብያተ-ክርስትያናት ጥገና ሚያዚያ ላይ ይጀመራል

አዲስ አበባ ጥቅምት 24 2013 (ኢዜአ) የላልይበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት ጥገና በመጭው ሚያዚያ ወር የሚጀመር መሆኑን የጥገና አስተባባሪ ኮሚቴው አስታወቀ፡፡

የአብያተ-ክርስቲያናቱን ጥገና ለማካሄድ በፈረንሣይና ኢትዮጵያ  ባለሙያዎች  ሲካሄድ የነበረው  ጥናት በኮቪደ 19 ምክንያት ተቋርጦ  ቢቆይም አሁን  መጀመሩ  ታውቋል።  

የኢትዮጵያ እና ፈረንሣይ ትብብር የቅርስ አድን ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር መንግስቱ ጎበዜ እንዳሉት የጥገና ስራው የጥናትና ምርምር እንዲሁም የትግበራ በሚል ተከፍሎ እየተሰራ ነው፡፡

የጥገና ስራው ከመጀመሩ በፊትም ከዚህ ቀደም በቅርሱ ዙሪያ የተሰሩ ስራዎች ለምን ውጤታማ ሳይሆኑ እንደቀሩ የሚፈትሽ ፍኖተ ካርታ መሰራቱንና በቅርሱ ዙሪያ ከዚህ ቀደም መፍትሄ ተብለው የተተገበሩት ለቅርሱ ሌላ ችግር ይዘው መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም አሁን ሊሰራ የታቀደው ዕድሳት በቀጥታ  ከሚጀመር ቅድሚያ ችግሩ  መታወቅ  ስላለበት ከፈረንሣይ እና ኢትዮጵያ የተወጣጡ ባለሙያዎች  ጥናት በመካሄድ  ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

የጥናት እና ምርምር ስራውን በአንድ ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ተጀምሮ እንደነበር አስታውሰው ኪቪድ 19 በመከሰቱ ምክንያት የፈረንሣይ ባለሙያዎች ባለመምጣታቸው የጥናትና ምርምር ስራው ባሣለፍነው ዓመት መጋቢት ወር ላይ መቋረጡን ተናግዋል፡፡

በዚህ የጥናትና ምርምር ጊዜም በርካታ የሰርቶ ማሳያ ስራዎች መሰራት ሲኖርባቸውም ሳይሠሩ መቅረታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ጥናቱ መጀመሩን አሥታውቀው በታህሣሥ ወር መጨረሻ ተጠናቆ ለትንተና እንደሚዘጋጅ ገልጸዋል፡፡

ጥናቱ ለ3 ወራት ተተንትኖ ከተዘጋጀ በኋላ በመጭው ሚያዚያ  ወር የዕድሳት ስራ  ይጀመራል  ነው ያሉት አስተባባሪው

ከ900 ዓመታት በላይ ዕድሜ እንዳስቆጠሩ የሚነገርላቸው የላልይበላ ውቅር አብያተ  ክርስቲያናት በዩኔስኮ የተመዘገቡ የዓለም ቅርስ መሆናቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም