"ኢትዮጵያን ለማፍረስ በሚሰሩ ኃይሎች ላይ መንግስት ጥብቅ እርምጃ መውሰድ አለበት"- የመከላከያ ሠራዊት የቀድሞ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
"ኢትዮጵያን ለማፍረስ በሚሰሩ ኃይሎች ላይ መንግስት ጥብቅ እርምጃ መውሰድ አለበት"- የመከላከያ ሠራዊት የቀድሞ አመራሮች
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 24/ 2013 (ኢዜአ) ህዝብን በማሸበር ኢትዮጵያን ለማፍረስ በሚሰሩ ኃይሎች ላይ መንግስት ጥብቅ እርምጃ መውሰድ መጀመር እንዳለበት የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የቀድሞ አመራሮች ተናገሩ።
የአገር መከላከያ ሠራዊት ተልዕኮን ለማስተጓጎል የሚሞክሩ ኃይሎችም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የቀድሞ የሰራዊቱ አመራሮቹ እንደሚሉት አገርን ለማፍረስ በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ላይ መንግስት ጥብቅ እርምጃ መውሰድ መጀመር አለበት።
መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እስካሁን የተከተላቸው አካሄዶች መልካም ቢሆኑም አንዳንዶች አጋጣሚውን አገር ለማፍረስ እየተጠቀሙበት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም መንግስት ለሃገርና ህዝብ ህልውና ሲል ወደ እርምጃ መግባት እንዳለበት በሠራዊቱ ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ሲያገለግሉ የነበሩት ኮሎኔል ተፈራ እሸቴ ተናግረዋል።
"በህዝብ ላይ የሚፈፀሙ እኩይ ተግባራትን ለማስቆም ሲባል በጥፋት አድራሾች ላይ ጥብቅ እርምጃ መውሰድ ግድ የሚልበት አጋጣሚ ላይ ተደርሷልም" ያሉት የቀድሞው አመራሩ "ህወሓትና ግንባር ፈጥረው የሚንቀሳቀሱ ሽፍቶች ዓላማቸው የተረጋጋ መንግስት እንዳይኖር በማድረግ አገር ማፍረስ በመሆኑ ከዚህ በኋላ በመንግስት በኩል ጥብቅ እርምጃ መውሰድ ይገባል" ብለዋል።
በጡረታ ላይ የሚገኙት ሻለቃ ወንዱ ወልዴም "በንጹሀን ዜጎች ላይ ግድያ መፈፀምን አይነተኛ አገር የማፍረሻ መንገድ አድርገው በቀጠሉ ኃይሎች ላይ መንግስት ጥብቅ እርምጃ መውሰድ መጀመር አለበት" ሲሉ ገልጸዋል።
እነዚህ ኃይሎች የመከላከያ ሠራዊቱን መልካም ስም የማጠልሸትና ተልእኮውን የማስተጓጎል ሥራ እያከናወኑ መሆኑንም አመልክተዋል።
"ለህገ መንግስቱ ተገዥ በመሆን የአገርን ሉአላዊነትና ዳር ድንበር የሚጠብቀውን የመከላከያ ሠራዊት ተልእኮ ማስተጓጎልም ተጀምሯል"፤ ይህም አገርን ለጠላት የሚያጋልጥና አደገኛ አካሄድ በመሆኑ ሊታለፍ የማይገባው ስህተት መሆኑንም የቀድሞዎቹ የመከላከያ አመራሮች ተናግረዋል።
በመሆኑም የአገር መከላከያ ሠራዊትን ተልእኮ ለማስተጓጎል የሚሞክሩ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ካልሆነም እርምጃ መውሰድ ይገባል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በህዝብ ግድያና ሽብር ፈጠራ ላይ ግንባር የፈጠሩት ኃይሎች ቀደም ሲል ባላንጣዎች እንደነበሩ ያስታወሱት ኮሎኔል ተፈራ፤ አገርን የማፍረስ አጀንዳ ይዘው መነሳታቸውን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ እየገጠሟት ላሉ የተለያዩ ፈተናዎች ዋናው ምክንያት ቀደም ሲል ስልጣን ላይ የነበረው ኃይል የፈጠረው ሴራ መሆኑንም ተናግረው፤ በቀጣይ የኢትዮጵያን ህልውና ለማስቀጠል የመንግስት ቆራጥ እርምጃ እንዳለ ሆኖ ህዝቡም ተደራጅቶ ሰላሙን በጋራ ማስጠበቅ እንዳለበት መክረዋል።