መንግስት በዜጎች ላይ ኢ- ሰብአዊ ድርጊት እንዳይፈጸም ጥበቃና ከለላ ሊያደርግ ይገባል- ቅዱስ ሲኖዶስ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት በዜጎች ላይ ኢ- ሰብአዊ ድርጊት እንዳይፈጸም ጥበቃና ከለላ ሊያደርግ ይገባል- ቅዱስ ሲኖዶስ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24/2013 ( ኢዜአ) መንግስት በዜጎች ላይ ኢ- ሰብአዊ ድርጊት እንዳይፈጸም ጥበቃና ከለላ ማድረግ እንደሚገባው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አሳሰበ።
ሲኖዶሱ በዜጎች ላይ ጥፋት የሚያደርሱ ወንጀለኞች ለፍርድ ሊቀርቡ ይገባል ብሏል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በኢትዮጵያ በምዕራብ ወለጋ እና በጉራፈርዳ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉምዝ የተገደሉ ዜጐችን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባስተላለፉት መልዕክት "እግዚአብሔር በፈጠረልን ምድር በየትኛውም አቅጣጫ ተከብረንና ተከባብረን እንድንኖር ምድርንም እንድናለማ ፈጥሮናል" ብለዋል።
የሰው ልጆች በዚህ ዓለም ላይ ሲኖሩ እንግዶች እንጂ ከመካከላቸው አንድም ባለአገር እንደሌለ ሊኖርም እንደማይችል የእግዚአብሔር ቃል እንደሚያስተምር በመግለጽ።
"እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ የሰው ልጅ በእጅጉ በተሳሳተ አመለካከት ውስጥ በመግባት ይሄ የኛ ያኛው የእናንተ አካባቢ እየተባባልን የመለያየት ሁሉ መሠረት የሆነውን የጠላትን መንፈስና አሠራር በመከተል እርስ በርሳችን በመጠላላት ወንድም ወንድሙን ሲያሳድድ እርስ በርሳችን እየተጠፋፋን እንገኛለን" ብለዋል።
ከትናንት በስቲያ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ከዛ በፊት በደቡብ ክልል ጉራፈርዳ እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በዓመታዊ ስብሰባ ላይ እያለ የሰማው ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል።
የተፈጸመው ተግባር ቅዱስ ሲኖዶሱንና ቤተ ክርስቲያንን በእጅጉ ያሳዘነ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዳወገዘው ነው ብፁዕነታቸው የጠቆሙት።
ሲኖዶሱ ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች በቤተክርስቲያኗ ስም መጽናናትን ይመኛል ብለዋል።
መንግስት በዜጎች ላይ ኢ- ሰብአዊ ድርጊት እንዳይፈጸምባቸው ጥበቃና ከለላ ማድረግ እንደሚገባውና ወንጀለኞችንም ለፍርድ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።
መልክ፣ቋንቋ፣ባህል፣አመለካከትና ስርዓት የጸጋ ስጦታ እንጂ የመለያያት ምክንያት ሊሆን አይገባም ነው ያሉት ቅዱስ ፓትሪያርኩ።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያዊያን በቀጣይ ለጋራ ሰላምና አንድነት እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።