ቀጥታ፡

የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ አባላትና ደጋፊዎቹን በማሳተፍ እንደሚታገል የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ

ሀዋሳ ጥቅምት 24/2013 (ኢዜአ) የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ መላው አባላትና ደጋፊዎቹን በማሳተፍ እንደሚታገል የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። 

ጽህፈት ቤቱ ባወጣው መግለጫ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በንፁሃን ዜጎች ላይ የኦነግሸኔ እና ህወሃት የጥፋት ሀይል  በንፁሐን ዜጎች ላይ የፈፀመውን ጥቃት  አውግዟል።

ይህ ሃይል ጊዜያዊ ጥምረትና ያልተቀደሰ  ጋብቻ በመመስረት  እኔ ካልመራሁ  ኢትዮጵያ  የምትባል ሀገር አትኑር በሚል   የጥፋት ሴራውን እንደቀጠለበት  አመልክቷል።

ለውጡ እንዲደናቀፍ ግጭትና ቀውስ መፍጠር መደበኛ ተግባሩ አደርጎ በመያዝና ያለ የሌለ ሀይሉን በመጠቀም ተስፋ ለማስቆረጥ ደፋ ቀና እያለ እንደሚገኝ  የፓርቲው  ጽህፈት ቤት በመግለጫው አስታውቀዋል።

የጥፋት ሀይሉ እየሰነዘረ ያለውን ጥቃት ተስፋ ሳንቆርጥ በብስለት፣ በጽናትና በጥንቃቄ መመከት ይስፈልጋል ብሏል።

የኋላ ታሪክ እንደሚያሳየው ንፁሀን ዜጎች ላይ ጥቃት በመፈፀም የሚገኝ የፓለቲካ ትርፍ ለማንም አይበጅም ያለው መግለጫው መላው የክልሉ ብሎም የሀገሪቱ ህዝቦች ከመንግስት ጎን በመሰለፍ የጥፋት ሀይሉን እኩይ ተግባር  ለመመከት  እንደተለመደው  ርብርብ እንዲያደርግ ጠይቋል።

ፓርቲው የህግ የበላይነት በማረጋገጥ የዜጎችን ሰላምና  ደህንነት የማስጠበቅ ስራ  ከወትሮው ተጠናክሮ እንዲቀጥል መላውን አባላትና ደጋፊዎቹን በማሳተፍ እንደሚታገል  አስታውቀዋል።

የብልጽግና ጉዟችን በጥፋት ሀይሎች እኩይ ተግባር አይደናቀፍም! ህብረ - ብሄራዊ አንድነታችን ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል!ም ብሏል።

የጥፋት ኃይሉ በንፁሐን ዜጎች ላይ ባደረሱት ጥቃት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን  በመግለጽ ለሟች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች ጨምሮለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም