አዲሱ ዓመት እና ዐበይት ኩነቶቹ - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ ዓመት እና ዐበይት ኩነቶቹ
በገዛኸኝ ደገፉ (ኢዜአ) የኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት ሲመጣ በብዙ ናፍቆት የሚጠበቅ ከመሆኑም ባሻገር በበርካታ ድምጻዊያን ዜማ በተለይም ደግሞ በአንጋፋው ድምጻዊ ክቡር ዶክተር ጥሁን ገሰሰ …“ክረምት አልፎ በጋ መስከረም ሲጠባ፤ አሮጌ አመት አልፎ አዲሱ ሲገባ…” በሚለውዜማ ይደምቃል።
አዲሱ ዓመት ሲገባ ለኢትዮጵያውያን የክረምቱ ጭጋግ፣ ዝናብና ጎርፍ አልፎ በጠራ ሰማይ የታጀበ ብርሃን የሚታይበት፣ የክረምትን ማለቅና የበጋን መጀመር የሚበሰርበት፣ አዳዲስ ዕቅድ የሚነደፍበት ወዘተ…በመሆኑ በተለየ ናፍቆት ይጠበቃል። አዲሱ ዓመት ያለፈውን በጎም ሆነ አሉታዊ ክስተቶች በትውስታ የሚታይበትና ወደ አዲስ እቅድና ዝግጅት ሽግግር የሚደረግበት “እንኳን አደረሰህ/ሽ” በመባባል መልካም ምኞት የሚለዋወጡበት ነው።
የዘንደሮው አዲስ ዓመት በዓለም አቀፍ እና በአገራችን የተከሰተው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በፈጠረው ድባብ የተለመደውን ያህል ድምቀት አልታየበትም። ወረርሽኙ በአገራችን መከሰቱን ተከትሎ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበረሰባዊ እና ስነ-ልቦናዊ ጫናዎችን አስከትሏል። በመላው ዓለም ላይ ጫና ያሳደረው የኮቪድ-19 ተጽዕኖ መቼ እንደሚጠፋ እንኳ ምንም ፍንጭ ሳይታይ ነው ወደ አዲሱ 2013 የተሻገርነው።
ሌላኛው ጉዳይ ባለፈው ዓመት መካሄድ የነበረበት አገር አቀፍ ምርጫ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት እንዲራዘም በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ውሳኔ መሰጠቱን ተከትሎ ውሳኔውን ባልተቀበሉ አንዳንድ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ከዘንድሮው መስከረም 30 በኋላ “መንግስት አይኖርም፤ አገሪቱ ወደ ብጥብጥ ታመራለች” በማለት ክረምቱን ሙሉ ሲሰራጩ በነበሩ ውዥንብሮች በብዙዎች ዘንድ ምን ሊፈጠር ይችል ይሆን? የሚል ስጋት መፍጠሩ ነው።
ኢትዮጵያ በእነዚህና መሰል ተደራራቢ ችግሮች ውስጥ ብታልፍም ከዘመን መለወጫ ዋዜማ ጀምሮ አዲስ የተስፋ ብርሃን ይዘው ብቅ ያሉ በርካታ አገር አቀፍ ኩነቶች ተከውነዋል። ለአብነት ለመጥቀስ ያህል አዲሱ ዓመት ገና ከመጀመሩ የአገሪቱን ገጽታ የሚቀይሩ ግዙፍ አገራዊ ፕሮጀክቶች ለምረቃ በቅተዋል፤ በርካታ አዳዲስ ፕሮጀክቶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተጀምረዋል። የማህበረሰቡ የአብሮነት እሴቶችን የሚያጎለብቱ ትላልቅ በዓላት ተከብረው ማለፋቸውም የኩነቶቹ ሌላው ገጽታ ነበሩ። ከዚህ ባሻገር ከወትሮው የተለየ ፖለቲካዊ አንድምታ የያዘው የዘንድሮው የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ የተካሄደበት በዚህም የዓመቱ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች የተመላከቱበት ነበር። ከአዲሱ ዓመት ጋር አብረው የመጡት እነዚህ ኩነቶች ከወትሮው የተለየ አገራዊ ትርጉም ያላቸው ናቸውና ጥቂቶቹን እንመልከት።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በይፋ መከፈት
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌዴሬሽን እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች አምስተኛ የፓርላማ ዘመን 6ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ 1ኛ መደበኛ የጋራ ስብሰባ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም ተካሂዷል። የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የዓመቱን የትኩረት አቅጣጫዎች የጠቆሙበትን ንግግር በማድረግ የሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ከፍተዋል። ይህ የዘንድሮው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ በልዩ ሁኔታ በጉጉት የተጠበቀ ነበር። ለዚህም እንደምክንያት የሚወሰደው የኮሮና ቫይረስ እያስከተለ ያለውን ጉዳት እና ቀጣይ ስጋት መነሻ በማድረግ በነሀሴ 2012 ዓ.ም ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው ሀገር አቀፍ ምርጫ መራዘሙ ነው።
የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት ስለምክር ቤቱ ስብሰባና የሥራ ዘመን የተደነገገውና አንቀጽ 58 ንኡስ አንቀጽ 3 ላይ የሰፈረው ሃሳብ “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው፤ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ይጠናቀቃል፡፡” ሲል ያስቀምጣል።
ከዚህ ቀደም ሲካሄዱ የነበሩት ምርጫዎች የኮቪድ-19 ወረርሽን የመሰሉ አገሪቱን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ እንድትገባ የሚያስገድድ ጉልህ እንቅፋቶች ባልነበሩባቸው ሁኔታዎች የተከናወኑ ናቸው። ከ2012 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሁም በኢትዮጵያ በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጣሉ ምርጫውን በተቀመጠለት መርሃ ግብር ማካሔድ እንደማይችል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ለኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሳወቁን ተከትሎ ጉዳዩ ህገ-መንግስታዊ ትርጉም እንዲሰጥበት ተደረጎ የምርጫው ጊዜ እንዲራዘም ተወስኗል።
የህገ-መንግስት ትርጉም አሰጣጥ ሂደቱና ምርጫው እንዲራዘም የተሰጠው ውሳኔ በክልሎችና በአብዛኛው የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ዘንድ ተቀባይነት የነበረው ቢሆንም የተወሰኑት ግን አልተቀበሉትም።
የምርጫ ጊዜ መራዘሙን ከተቃወሙት መካከል የህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) አንዱ ነው። የህወሃት መከራከሪያ በህገመንግስቱ የምክር ቤቶች የስልጣን ዘመን አምስት ዓመት መሆኑን በግልጽ በመደንገጉ ምርጫን ለማራዘም ህገ መንግስቱን መተርጎም አያስፈልግም የሚል ነው። በዚህም መሰረት ህወሃት የኮቪድ-19ን ተጽእኖ እየተከላከሉ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል በማለት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ህጋዊ መሰረት የለውም ብሏል። በዚህ አቋሙ በመቀጠልም በክልሉ የምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም ጳጉሜ 4 ቀን 2012 ዓ.ም ክልላዊ ምርጫ አካሂዷል። ሆኖም በሕገ መንግሥት አንቀጽ 102 (1) መሰረት በመላ አገሪቱ በፌዴራልም ሆነ በክልሎች የሚደረጉ ምርጫዎችን የማስፈጸም ሥልጣን የተሰጠው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መሆኑን ይደነግጋል።
የፌዴሬሽን ም/ቤት በትግራይ ክልል የተካሄደው ምርጫ ም/ቤቱ ሀገራዊውን ምርጫ ለማራዘም ያሳለፈውን ውሳኔ ባለመቀበል የተከናወነ መሆኑን በመጥቀስ ክልላዊ ምርጫው እና ሂደቶቹ በሙሉ ህገ ወጥ መሆናቸውን በመግለጽ እንዳልተደረጉ የሚቆጠሩ፣ የማይጸኑ እና ተፈጻሚነት የሌላቸው ናቸው ሲል ውሳኔ አሳልፏል። በዚህ ምክንያት ህወሃት ከፌዴራል መንግስት ጋር እሰጣገባ ውስጥ ገብቷል። ህወሃት በተደጋጋሚ እንደሚገልጸው የፌዴሬሽን እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች የስልጣን ዘመናቸው ስላጠናቀቁ “ፓርላማው ከመስከረም 30 በኋላ የስልጣን ጊዜው ስለሚያበቃ” ማንኛውም ውሳኔ ማስተላለፍ አይችልም። ይህ ተቃርኖ በፌዴራል መንግስትና በህወሃት መካከል የተካረረ ልዩነት ከመፍጠሩም በላይ እስካሁንም ውዝግቡ መቋጫ ላይ አልደረሰም። በዚህ ምክንያት የዘንድሮው የሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ምክርቤት ስብሰባ ህብረተሰቡ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል።
በአገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን የአገሪቱን ሰላም ለማወክ የሚጥሩ አካላትን ተቃውመዋል። «ኢትዮጵያ ነበረች፣ አለች ትኖራለች!» እና “መስከረም 30 የኢትዮጵያዊነት ድምጽ” በሚሉ መሪ ሀሳቦች በሰሜን አሜሪካ አትላንታ ጆርጂያ፣ ሎስ አንጀለስ፣ ካሊፎርኒያ፣ ዳላስ ቴክሳስ፣ ሲያትል፣ ዋሽንግተን ዲሲና ሜኒሶታ ግዛቶች፣ እንዲሁም በአውሮጳ በእንግሊዝ፣ በጣሊያን፣ በኖርዌይና በአውስትራሊያ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በጋራ በመሰባሰብና የበይነ መረብና ሌሎች የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመጠቀም ልዩ ልዩ መልእክቶችንና መፈክሮችን በመያዝ ሠላማዊ ሠልፍ አካሂደዋል። የጸጥታ አስከባሪ ተቋማትም ከመስከረም 30 ቀን 2013 በኋላ “ህጋዊ መንግስት የለም” በሚል አገራዊ ትርምስ ለመፍጠር በሚሰሩ አካላት ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወሰድ በጥብቅ አሳስቧል።
ከመደበኛ ስራው ለአፍታም ቢሆን ያልተዘናጋው መንግስት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሃላፊነቶቹን እየተወጣ ይገኛል። የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም የጋራ ስብሰባ ባካሄዱበት የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የዓመቱ ዋና ዋና የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎችን አብራርተዋል። ሰላምና ጸጥታ፣ የህግ የበለይነት፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት እንዲሁም የግብርና ምርታማነት የመሳሰሉት ከአንኳር ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ።
የወዳጅነት አደባባይ ፕሮጄክት
በአዲሱ ዓመት መግቢያ ዐበይት ኩነት ከነበሩት መካከል አንዱ በዋዜማው ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ለምረቃ የበቃው የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት አካል የሆነው የወዳጅነት አደባባይ ነው። ይህ የወዳጅነት አደባባይ ተጠናቅቆ ለምረቃ መብቃቱ አዲሱን ዓመት ያደመቀና የኢትዮጵያውያንን ተስፋ ያነሳሳ ነበር። ፓርኩ በአራት ኪሎ ከሸራተን ሆቴል ፊት ለፊት ያለውን 42 ስኩዌር ኪሎ ሜትር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን ፕሮጀክቱ በውስጡ ሰው ሰራሽ ሃይቅ፣ የሥነ ጥበብ ማቅረቢያ ስፍራ፣ የህፃናት መዝናኛ፣ የአበባ መናፈሻ እንዲሁም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከላትን ያካተተ ነው። ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት ኢትዮጵያውያን ገንዘብ በማዋጣት አሻራቸውን በማኖር የጀመሩት ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑ ይታወሳል።
አዲስ አበባ ከፌዴራል መንግስት መቀመጫነቷ ባሻገር የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ መጠን የወዳጅነት ፓርክ ከኢትዮጵያውያን አልፎ አፍሪካውያን የሚኮሩባት ብሎም አገራችን ስሟንና ደረጃዋን ከፍ የሚያደርግ ነው። ፕሮጀክቱ ዘመን ተሻጋሪ እንደመሆኑ መጠን በዜጎች ዘንድ አዲስ ተስፋን የፈጠረና ለኢትዮጵያውያንና ለአፍሪካውያን የመተባበርን ትርጉም አጉልቶ ያሳየ ነው። ይህ ፓርክ ብቻ ከአራት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የእንጦጦ ፓርክ
የአዲሱ ዓመት መግባትን ተከትሎ ለምረቃ የበቃው ሌላኛው ግዙፍ ፕሮጀክት ሃገርኛ ስያሜዎችን እና መዝናኛ ዘርፎችን ባካተተ መንገድ የተገነባውና ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት አካል የሆነው የእንጦጦ ፓርክ ነው። የእንጦጦ ፕሮጀክት አገር በቀል ዕውቀቶችንና ግብዓቶችን ጥቅም ላይ በማዋል የተገነባ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ከተባበሩ አገርን የሚለውጡ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ እንደሚችሉ ፓርኩ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል። ፓርኩ በተለያዩ አገር በቀል ዛፎች የተከበበ በመሆኑ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው ካለው ጠቀሜታ ባለፈ በአጭር ጊዜ ትልቅ ፕሮጀክትን በማጠናቀቅ የሥራ ባህልን መቀየር የተቻለበት አጋጣሚ መሆኑንም በምረቃው ወቅት ተገልጿል።
ፓርኩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መስከረም 30 ቀን 2013 ተመርቆ ለጎብኝዎች ክፍት ሆኗል። በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያን ለመቀየር የሚስፈልገው ትብብር መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በፓርኩ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ከ460 በላይ በአካባቢው የሚገኙ እናቶችም የስራ መስሪያ ቦታቸውን ቁልፍ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ተረክበዋል፡፡
ገበታ ለሃገር ፕሮጀክቶች
የአዲስ አበባን ገጽታ ይቀይራል ተብሎ ከሚታሰበው “ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት” ልምድ በመውሰድ ወደ አገር አቀፍ ፕሮጀክት ሽግግር መደረጉን ይፋ የተደረገውም የአደሱ ዓመት መግባትን ተከትሎ ነው። በዚሁ መሰረት በደቡብ ክልል የኮይሻ፣ በኦሮሚያ ክልል የወንጪ እና በአማራ ክልል የጎርጎራ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች እንደሚሰሩ ይፋ ተደርጎ የገቢ ማሰባሰብ ስራ እየተሰራ ይገኛል።
እነዚህ የገበታ ለሃገር ፕሮጀክቶች በየአካባቢው ትኩረት ሳያገኙ የቆዩ ሲሆን ተገንብተው ስራ ሲጀምሩ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ለኢትዮጵያ እድገት ወሳኝ ድርሻ እንደሚነራቸው ይታመናል። የፕሮጀክቶቹ መጀመር በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ የፈጠረው ደስታና መነቃቃት ወደር የለውም። የልማት ስራዎቹ ከሚፈጥሩት የስራ ዕድል ባሻገር የየአካባቢውን የተፈጥሮ ፀጋ ለዓለም ማህበረሰብ በማስተዋወቅ ለሀገር ገፅታ ግንባታና እድገት የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ግልጽ ነው።
ፕሮጀክቱ በአፋጣኝ ተግባራዊ እንዲሆኑም ኢትዮጰያውያን አሻራቸውን ማኖር ጀምረዋል። የመንግስት ሠራተኞች ከወር ደመወዛቸው እየለገሱ ሲሆን የተለያዩ ተቋማትና ድርጅቶችም ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛል። ይህን መሰል የልማት ፕሮጀክቶች በየአካባቢው እየሰፉ መምጣት በመንግስትና በህዝብ መካከል መተማመን በመፍጠር የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ እንደሚያፋጥን ብዙዎች ይናገራሉ።
አዳዲስ የብር ኖቶች
የአዲሱ ዓመት መግቢያ ተከትሎ ሌላኛው ጉልህ ኩነት ነባሮቹ የገንዘብ ኖቶች በአዳዲስ የመተካቱ ክስተት ነው። የአዲሱ የገንዘብ ኖት አምስት ብርን ሳይጨምር በሌሎች ኖቶች ላይ ለውጥን አስከትሏል። ከዚህ ባሻገር በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለ 200 ብር ኖት ወደ ገበያ ገብቷል። ይህ ኩነት ያልተጠበቀና በድንገት የተነገረ በመሆኑ ብዙዎች በአዎንታ፣ ሌሎች ደግሞ በአሉታዊና በስጋት መልክ የተለያዩ ትንታኔዎችን የሰጡበት ነበር።
አዲሱ የብር ኖት ለውጥ ያስፈለገበት ዐበይት ምክንያት በአገሪቱ ከባንክ ውጭ የሚንቀሳቀስ በቢሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ በመኖሩ ወደ ባንክ ስርዓት ለማስገባት እንደሆነ መንግስት አሳውቋል። ከዚህ በተጨማሪ በህገ ወጥ መንገድ የሚታተሙ የገንዘብ ኖቶችን እንዲሁም ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር ያለመ እንደሆነም ተገልጿል።
ይህ የብር ኖት ለውጥ የግለሰቦች ቁጠባ ባህልን ለማሻሻል፣ የባንኮችን የማበደር አቅም ለማሳደግና የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ዓይነተኛ ሚና እንደሚኖረው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በሌላ አገላለጽ ባንኮች የማበደር አቅም ስለሚኖራቸው ኢንቨስትመንትን ያነቃቃል፤ ኢኮኖሚው እንዲያድግ ያደርጋል፣ የስራ እድልንም ይፈጥራል ማለት ነው።
አሮጌው የብር ኖት በአዲሱ መተካቱን ተከትሎ በሚሊዮን የሚቆጠር አዳዲስ የባንክ አካውንት የተከፈቱ ከመሆኑ በተጨማሪ ከባንክ ውጪ በግለሰቦች እጅ ተከማችቶ የነበረ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ወደ ባንክ እንዲገባ ተደርጓል። ይህም እንደዘርፉ ባለሙያዎች አገላለጽ ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ ያደርጋል።
በዩኔስኮ የተመዘገቡ በዓላት አከባበር
ሌላኛው ኩነት አገሪቷ በማይዳሰስ ቅርስነት ለአለም የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ ካስመዘገበቻቸው በአላት መካከል ከወርሃ መስከረም አጋማሽ በኋላ የሚከበሩት የመስቀል እና የኢሬቻ በአላት ሲሆኑ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መስፋፋት ስጋት ምክንያት እንደተለመደው በርካታ ሰዎች በተገኙበት አልተከበሩም። ሆኖም ግን ውስን ሰዎች በተሳተፉበትና ከፍተኛ ጥንቃቄ በተደረገበት መልኩ በሰላምና በድምቀት ተከብሯል። ሁለቱ በዓላት የአብሮነት እሴቶችን በማጎልበት ረገድ የሚያበረክቱት ድርሻ ከፍተኛ ነው።
መስከረም 25 ላይ ተጀምሮ እስከ መስከረም 30 በሚዘልቅ አርማጌዶናዊ የእርስ በእርስ ጦርነት የኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት አብቅቶ ኢትዮጵያ የተባለችው ሃገር ወደ መንግስት አልባ ሃገራት ዝርዝር ውስጥ ተመዝግባ የምስራቅ አፍሪካ ሌላኛዋ የትርምስ ማእከል ትሆናለች የሚል ምኞት የነበራቸው አካላት ቢኖሩም ትንቢቶቹ ሳይፈጸሙ አገር ተረጋግታ ቀጥላለች። ህጻናቱና ታዳጊ ወጣቶቹ ወደ ትምህርት ገበታቸው ሊመለሱ ቀናት ብቻ ቀርተዋል።
አዲሱ ዓመት እንዲህ እንዲያ እያለ የጀመረ ሲሆን እንደ አመጣጡ የተሸኘው ወርሃ መስከረም ያለፈው ወር ከተባለ ቀናት አልፈው ሳምንታትን ያስቆጠረ ሲሆን ህይወትም በተለመደው ምህዋሯ እየዞረች ሃምሌና ነሃሴ ላይ ሰዓት ሳይጠብቅ ይወርድ የነበረው ዝናብና አላንቀሳቅስ ሲል የነበረው ጭቃና ጎርፍ አልፎ በመስከረም ወር የተጀመረው አዲስ የተስፋ ብርሃን አሁንም ቀጥሏል።