ቀጥታ፡

በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሚገኙ ዲፕሎማቶች ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የአንድ ወር ደመወዛቸውን ሰጡ

አዲስ አበባ ጥቅምት 24/2013 (ኢዜአ) በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሚገኙ ዲፕሎማቶች ለገበታ ለሀገር የአንድ ወር ደመወዛቸውን ሰጥተዋል።

የኤምባሲው ዲፕሎማቶች የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለፕሮጀክቱ መስጠታቸውን በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም ለኢዜአ ገልጸዋል።

በአገራዊ የልማት እንቅስቃሴዎች ዲፕሎማቱ ድጋፍ የሚያሰባስብ ብቻ ሳይሆን ራሱም አስተዋጽኦ የማበርከት ኃላፊነት አለበት ብለዋል።

ኤምባሲው በኬንያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚያስችል ስራ መጀመሩንና ይሄም በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።

በኬንያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለመደገፍ የቦንድ ግዢ እያከናወኑ እንደሚገኙም አምባሳደር መለስ የገለጹት።

በኬንያና በማላዊ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሕዳሴ ግድብ የቦንድ ሽያጭ፣ ቃል የማስገባትና በግድቡ ዙሪያ ያተኮረ ውይይት እሁድ ጥቅምት 29 ቀን 2013 ዓ.ም የበይነ መረብ ውይይት እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአማራ ክልል ጎርጎራ፣ በኦሮሚያ ክልል ወንጪና በደቡብ ክልል ኮይሻ የሚገኙ አካባቢዎችን ለማልማት በነሐሴ 2012 ዓ.ም የ“ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክትን ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።

ለሦስቱ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ቢያንስ 6 ቢሊዮን ብር የሚያስፈልግ ሲሆን ከባለሃብቶች፣ ከኅብረተሰቡና ከዳያስፖራው ሦስት ቢሊዮን ብር ይሰባሰባል ተብሎ ይጠበቃል።

ቀሪውን ገንዘብ ደግሞ ከልማት አጋሮች ለመሰብሰብ ታቅዷል።

የመንግስት ሠራተኞችና ተቋማት፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ ዳያስፖራዎችና ግለሰቦች ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም