ምክር ቤቱ የንፁሃን ዜጎችን ህይወት ባጠፉ ኃይሎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የንፁሃን ዜጎችን ህይወት ባጠፉ ኃይሎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አሳሰበ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24/2013 ( ኢዜአ) መንግስት የንፁሃንን ህይወት እያጠፉ ባሉ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወስድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።
ምክር ቤቱ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ባሉ የወንጀል ድርጊቶች ላይ ሰፊ ውይይት አካሂዷል።
ምክር ቤቱ ዛሬ የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ለመወያየት የተሰበሰበ ቢሆንም በአባላቱ ጥያቄ መሰረት በንፁሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ቅድሚያ እንዲሰጠው ተደርጓል።
ይህን ተከትሎ ምክር ቤቱ በመተከል፣ በጉራፈርዳ፣ በወለጋ በተፈጸሙ ጥቃቶችና ከደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ የታገቱ ተማሪዎችን ጨምሮ በንፁሃን ዜጎች ላይ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ላይ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስዶ ተወያይቷል፡፡
ይህንንም ተከትሎ የምክር ቤቱ አባላት መንግስት ድርጊቱን የፈጸሙ አካላት ከዚህ በኋላ በድርጊታቸው እንዲቀጥሉ መፍቀድ የለበትም ብለዋል።
ድርጊቱን እየፈጸሙ ያሉ አካላትን የተመለከቱ መረጃዎችን ለምክር ቤቱ በማቅረብ ጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት እልባት እንዲያገኝ ሃላፊነቱን መወጣት አለበት ሲሉም ጠይቀዋል።
አባላቱ እየተፈፀመ ያለው ብሄር ተኮር ጥቃት በመላው ኢትዮጵያዊ ላይ የተፈፀመና የሁሉንም ልብ የሰበረ በመሆኑ በአንድ ላይ እንቆማለን ብለዋል።
ሁላችንም ማንኛውንም ዋጋ በመክፈል የኢትዮጵያን አንድነት ማስቀጠል አለብን በማለትም አቋማቸውን አንፀባርቀዋል።
ይህ ሲሆን ግን በጥንቃቄና የጥፋት ኃይሎቹን ዓላማ በማያስፈጽም መልኩ መሆን እንዳለበት ነው የመከሩት፡፡
ምክር ቤቱ በቀጣይ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እንደሚያደርግም ተገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ምክር ቤቱ ወደ ቦታው ልዑክ በመላክ ጉዳዩን እንደሚያጣራና በትኩረት እንደሚከታተል አስታውቋል፡፡
መንግስት በጉዳዩ ላይ የሚሰራቸውን ስራዎች በተመለከተ አስፈጻሚው አካል ማብራሪያ እንዲሰጥ በአጀንዳነት እንደሚያዝም ተገልጿል፡፡
ምክር ቤቱ አስፈፃሚው አካል የሚያደርጋቸውን ተግባራት የመደገፍ፣ የመከታተልና የመቆጣጠር ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናግረዋል።
መላው የኢትዮጵያ ህዝብም ከመንግስት ጎን ቆሞ ጥቃቱን የማስቆሙን ስራ እንዲደግፍ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ምክር ቤቱ ከዚህ ውይይት በኋላ ሶስት አዋጆችን መርምሮ ለቀጣይ እይታ ወደ ሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች አስተላልፏል።
በዚህም መሰረት የግብርና ምርት ውል ረቂቅ አዋጅ ለግብርና፣አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተመራ ሲሆን ፣የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ረቂቅ አዋጅ የግልግል ዳኝነትና የእርቅ አሰራር ስርዓትን ለመደንገግ የወጣ ረቂቅ አዋጆች ደግሞ ለሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ተመርተዋል።
ምክር ቤቱ በዛሬው ስብሰባ በተለያየ ምክንያት ከሰብሳቢነት የተነሱ የቋሚ ኮሚቴ አመራሮችን አሟልቷል።
በዚህም መሰረት ወይዘሮ ያዬሽ ተስፋሁነኝ የገቢ በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ፣ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ አቶ አቡ ብርኪ የህግ የፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ሆነው ተሹመዋል።