ብሄር፣ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በጥፋት ኃይሎች ላይ ለሚወስደው እርምጃ ከመንግስት ጐን እንዲቆሙ ምክር ቤቱ ጥሪ አቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ብሄር፣ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በጥፋት ኃይሎች ላይ ለሚወስደው እርምጃ ከመንግስት ጐን እንዲቆሙ ምክር ቤቱ ጥሪ አቀረበ
ጥቅምት 24/2013 (ኢዜአ) ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች መንግስት በጥፋት ኃይሎችና አሸባሪዎች ላይ ለሚወስደው እርምጃ ከመንግስት ጐን እንዲቆሙና አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በማህበራዊ ድህረ ገጹ እንደገለጸው ምክር ቤቱ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ዋጋ ቃንቃ ቀበሌ በንፁሀን ዜጐች ላይ በደረሰው አሰቃቂ ጥቃት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገልጿል።
“ይህን መሠል ወንጀል በተደጋጋሚ እየተፈፀመ የዜጐቻችንን ህይወት እየቀጠፈም ይገኛል” ያለው ምክር ቤቱ፤ በመሆኑም ስለሀገርና ስለሰው ልጆች ክብርና ስብዕና በሌላቸው የጥፋት ሃይሎች ላይ መንግስት የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንዳለበት አስገንዝቧል።
የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች መንግስት በጥፋት ኃይሎችና አሸባሪዎች ላይ ለሚወስደው እርምጃ ከመንግስት ጐን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪውን አስተላልፏል።
ምክር ቤቱ ለተጎጂ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያውያን መጽናናትን ተመኝቷል።