ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አዲስ አበባ የራሷ ሊቀ ጳጳስ እንዲኖራት ወሰነች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 23/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አዲስ አበባ የራሷ ሊቀ ጳጳስ እንዲኖራት ወሰነች፡፡

ቤተክርስቲያኗ ፈጣሪ ኢትዮጵያን እየታየ ካለው ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ እንዲታደግ ከህዳር 1 እስከ 7 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ጸሎተ ምህላ እንዲደረግ ለምዕመናን መልዕክት አስተላልፋለች። 

ላለፉት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ 39ኛ አጠቃላይ  ምልዓተ-ጉባዔ ጸሎተ ምህላን ጨምሮ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ መጠናቀቁን አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ተሰጥቷል፡፡

የቤተ ክርስቲያኗ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸኃፊና የምስራቅ ጎጃም ሐገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአዲስ አበባ ከተማ እንደ ማንኛውም ሐገረ ስብከት የራሷ ሊቀ ጳጳስ ተመድቦላት እንድትመራ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

"የአዲስ አበባ ከተማ ሐገረ ስብከትን ለማዋቀር ከህግ-ባለሙያ ጋር ህጉን አሻሽለው ለግንቦቱ ርክበ ካህናት እንዲያቀርቡ ሶስት ብጹዓን አባቶችን ጉባኤ መድቧል" ብለዋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ያስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት አልያም በሞግዚትነት ለማስተዳደር እንደተደረገ ሙከራ አድርጎ እንደሚያየውና በጽኑ እንደሚያወግዘው ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ቤተ-ክህነት አደራጅ ነን ከሚሉ አካላት ጋርም ውይይት ተደርጎ ከመግባባት በመደረሱ ሥልጣነ ክህነታቸው ተለቆ በቤተ-ክርስቲያኗ መዋቅር ተመድበው እንዲያገለግሉ መወሰኑንም አስረድተዋል፡፡

ወቅታዊ አገራዊ ጉዳይን በሚመለከትም የእርቅና የሰላም ሂደቱን የሚያስፈጽሙ ብፁዓን አባቶችን በአስታራቂነት መሰየማቸውንም አቡነ ዮሴፍ አስታውቀዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያኗና በምዕመኗ የሚደርሰው ግፍና መከራ እንዲቆም፣ የታሰሩ ካህናትና ምዕመናን ጉዳያቸው ታይቶ መፍትሔ እንዲያገኝ ሲኖዶሱ መጠየቁን ገልጸዋል፡፡

በቤተክርስቲያኗ ላይ ለሚደርሰው ጥፋት ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት በሕግ እንዲጠየቁም  አሳስባለች ፡፡

ምዕመናን በተለየየ ምክንያት ችግር ላይ ለወደቁ ወገኖች ድጋፍ እንዲያደርጉ ቤተ ክርስቲያኗ ጥሪዋን አቅርባለች፡፡

ቤተክርስቲያኗ ፈጣሪ ኢትዮጵያን እየታየ ካለው ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ እንዲታደግ ከህዳር 1 እስከ 7 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ጸሎተ ምህላ እንዲደረግ ለምዕመናን መልዕክት አስተላልፋለች። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም