ከሐረማያ ሐይቅ ለእርሻ የሚሳበው ልቅ የውሃ አጠቃቀምና እንክብካቤ ጉድለት በሀብቱ ላይ ስጋት ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
ከሐረማያ ሐይቅ ለእርሻ የሚሳበው ልቅ የውሃ አጠቃቀምና እንክብካቤ ጉድለት በሀብቱ ላይ ስጋት ፈጥሯል
ሐረር፣ ጥቅምት 23 ቀን 2013(ኢዜአ) ከሐረማያ ሐይቅ ለእርሻ የሚሳበው ልቅ የሆነ የውሃ አጠቃቀም እና የእንክብካቤ ጉድለት ውሃው ለመድረቅ ስጋት እንደፈጠረበት የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ሐይቁ ያለበትን ስጋት መከላከል በሚቻልበት ዙሪያ ከአካባቢው ማህበረሰቡና ባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።
በዚህ ወቅት ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ ሐይቁን አውቀዋለው ያሉት የአካባቢው ነዋሪ መምህር አብዲ ጠሊል ከ20 ዓመት በኋላ የተመለሰው የሐረማያ ሐይቅ በአካባቢው በሚከናወኑ ልቅ የውሃ አጠቃቀም የመድረቅ ስጋት እንዳለበት ገልጸዋል።
በተለይ ጠዋት ብዛት ያላቸው የውሃ ማጓጓዣ የቦቴ ተሽከርካሪዎችና በሐይቁ ዳርቻ ያሉ ከ200 በላይ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ለእርሻ በሚስቡት ልቅ የውሃ አጠቃቀም ሐይቁ ስጋት ውስጥ ይገኛል ብለዋል።
"በሐይቁ መመለስ እንደተደሰትን ደርቆ እንዳናዝን በውሃ አጠቃቀሙ ላይ የከተማው አስተዳደርና ዩኒቨርሲቲው የህብረተሰቡን ግንዛቤ የመቀየር ስራ መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።
በሐይቁ ዳርቻ ለእርሻ ስራ በሞተር ከሚሳበው ከፍተኛ የውሃ መጠን በተጨማሪ ህብረተሰቡ በሐይቁ ላይ የሚጣለው ደረቅ ቆሻሻ ሀብቱን እየጎዳ አሳሳቢ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አቶ መሀመድ አብዱረሃማን ናቸው።
ለምግብነት እየዋሉ የሚገኙት ዓሳዎች ላይ ስጋት እየፈጠረ ስለሚገኝ ከተማ አስተዳደሩ የደረቅ ቆሻሻ ማከማቻና ማስወገጃ ስፍራዎችን በማዘጋጀት ሐይቁን መታደግ ይገባዋል ብለዋል::
ሐይቁ በመመለሱ በአሳ ንግድና በጀልባ የመዝናኛ ስራ እየሰራው እገኛለው ያለው ወጣት ሐጂብ አሊ በበኩሉ በተለይ ማህበረሰቡ በሐይቁ ዳርቻ ላይ የሚጥለው ቆሻሻ አካባቢውን ከመበከሉ ባለፈ ሐይቁ በደለል እየተሞላ መሆኑን ገልጿል።
"ሐይቁን ለመታደግ ብንጥርም መፍትሄ ማግኘት አልቻልንም" ያለው ወጣቱ በቀጣይ ከተማ አስተዳደሩ የህዝብ ንቅናቄን በመፍጠርና በጀት በመመደብ መስራት እንዳለበት አስተያየቱን ሰጥቷል።
የሐረማያ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ጽህፈት ቤት ሓላፊ ወይዘሪት ሂክመት አደም በበኩላቸው ከ20 ዓመት በኋላ ተመልሶ የመጣው የሐረማያ ሃይቅ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ወደ 200 ለሚጠጉ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
ሆኖም ከውሃ አጠቃቀም አንጻር ስጋት እያሳደረ እንደሚገኝ አረጋግጠው ችግሩን ለማቃለል የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑንና ይህም በአጭር ጊዜ ተግባራዊ በማድረግ ሐይቁን የመታደግ ስራ ይከናወናል ብለዋል።
ከደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ጋር በተያያዘ በከተማ አስተዳደሩ፣ መንግስትና ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ሁለት የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ በተያዘው በጀት ዓመት እንደሚገነባም ጠቁመዋል።
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አብዱለጢፍ አህመድ ለሐይቁ መመለስ ዘንድሮው የጣለው ዝናብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅትም ከአጠቃቀም አንጻር የሚታየው ሁኔታ ስጋት መፍጠሩን ተናግረዋል።
ሐይቁን ለማቆየት ዩኒቨርሲቲው ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በአጠቃቀም ዙሪያ በመነጋገር ለዚህም የህግ ማዕቀፍ ስራ እንደሚመቻች ገልጸዋል።
ከ20 ዓመት በፊት 11 ሜትር ጥልቀት የነበረው የሐረማያ ሐይቅ በአሁኑ ወቅት 4 ሜትር ጥልቀት ያለው ውሃ በመያዝ በአካባቢው ለሚገኙ ማህበረሰብ የመዝናኛ አገልግሎት እንዲሁም በዓሳ ልማት ፣በጀልባና ዋና ልብስ ኪራይ ለወጣቶች የስራ እድል እንደፈጠረ ተመልክቷል።