ቀጥታ፡

ታዋቂው የሆሊዉድ የፊልም ተዋናይ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚገመት የአልባሳት ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 23/2013(ኢዜአ) ታዋቂው የሆሊዉድ የፊልም ተዋናይ ታይለር ፔሪ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚገመት አልባሳት በኢትዮጵያ ለተቸገሩ ሴቶችና ህጻናት ድጋፍ አደረገ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አልባሳቱን በነጻ በማጓጓዝ ሲተባበር ፣የጉምሩክ ኮሚሽን ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ አድርገዋል።  

ትውልደ ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊው ዮናስ ጂ. ዓለሙ ድጋፉን በማስተባበር ለሴቶች ፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ዛሬ አስረክቧል።  

ሚኒስቴሩም አልባሳቱን ለሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ የልማት ድርጅት ተወካይ ሰጥቷል።

''እኛ ስንዋደድና ስንተሳሰብ ዓለም ያስብልናል''ያሉት አቶ ዮናስ፣ ኢትዮጵያን የሚወደው ታዋቂው የፊልም ተዋናይ ድጋፉን በማድረጉ እንዲሁም አየር መንገዱ ላደረገው ትብብር ምስጋናውን አቅርቧል።

በቀጣይም ዳያስፖራውን ማህበረሰብ በማስተባበር የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ለማከናወን ማቀዳቸውንም ገልጸዋል።

የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ ፣ድጋፉን ላደረገው አሜሪካዊ ተዋናይ ታይለር ፔሪና ድጋፉን ላስተባበሩ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ  መንግሥት ከድህነት ለመውጣት ጥረት እያደረገ መሆኑንና 70 በመቶ ያህል ዜጎቿ ወጣት የሆነች አገርን ከድህነት ለማውጣት በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።

የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መስራች ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ በዚሁ ወቅት ድጋፉን ላደረገው በጎ አድራጊና  ድጋፉን አስተባብረው ያደረሱ አካላትን አመስግነዋል ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቱሪዝም ሽያጭ  ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ቃኘው ፍሥሐ፣ አየር መንገዱ የሕዝብ ንብረት እንደመሆኑ በቀጣይም መሰል የበጎ አድራጎት ተግባራትን ያከናውናል ብለዋል።  

አሜሪካዊው ታይለር ፔሪ ከተዋናይነት ሙያው ባሻገር፤ፀሐፊ፣አዘጋጅና ዳይሬክተር ሆኖ የሚሰራ የ51 ዓመት ዕድሜ ጎልማሳ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም