አገራዊ ለውጡ መስመሩን እንዳይስት ለማድረግ የመንግስት የተጠና እና ስልታዊ እርምጃ ወሳኝ ነው- የቀድሞ የፓርላማ አባላት - ኢዜአ አማርኛ
አገራዊ ለውጡ መስመሩን እንዳይስት ለማድረግ የመንግስት የተጠና እና ስልታዊ እርምጃ ወሳኝ ነው- የቀድሞ የፓርላማ አባላት
አዲስ አበባ ጥቅምት 23/2013 (ኢዜአ) አገራዊ ለውጡ መስመሩን እንዳይስት መንግስት ስልታዊና የተጠና እርምጃ እየወሰደ ማስቀጠል እንዳለበት ኢዜአ ያነጋገራቸው የቀድሞ የህዝብ ተወካዮች መክር ቤት አባላት ገለጹ።
ተወካዮቹ ከ1998 እስከ 2002 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆን አገልግለዋል።
አሁን በአገሪቱ የተጀመረው ለውጥ በብዙ ጥረትና ጥበባዊ አካሄድ የመጣ መሆኑን የገለጹት የምክር ቤቱ አባላት በተለያዩ አደናቃፊ ሃይሎች ሃዲዱን እንዳይስት ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ለዚህም መንግስት ስልታዊና የተጠኑ እርምጃዎችን እየወሰደ ለውጡን ማስቀጠልና የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ እውን ማድረግ አለበት ነው ያሉት።
ለተጀመረው የለውጥ ስኬት የህዝቡ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው አባላቱ የድርሻቸውን ድጋፍና እገዛ ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።
ለውጡን እየመራው ያለው የመንግሰት አካልም "በስሩ ተሰግስገው አገር ለማፍረስና ለውጡን ለማደናቀፍ" የሚሰሩትን ለይቶ መዋቅሩን ማጥራት አለበት ብለዋል።
ቀድሞ የህዝብ ተወካዮች መክር ቤት አባላት መካከል አቶ አንዱአለም አያሌው እንደሚሉት በጥበብና የአገርን ህልውና ባስጠበቀ መልኩ የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል የመንግስት የተጠና እርምጃና ስልታዊ አመራር መጠናከር አለበት።
የኢትዮጵያን ህልውና ለማናጋት የሚጥሩ ቡድኖች ላይም የመንግስት እርምጃ ያስፈልጋል ይላሉ።
በተለይ ደግሞ ማንነትንና ብሔረን መሰረት አድርገው የሚፈጸሙ ጥቃቶች አገርን ለከፋ ችግር ሊዳርጉ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ያሻዋል ብለዋል።
ሌላው የቀድሞ የምክር ቤት አባል አቶ ኡመር አህመድም የተገኘውን ለውጥ ለማስጠበቅ በትብብርና በአንድነት መስራትን ይጠይቃል ብለዋል።
በመንግስት መዋቅር ውስጥ "ተሰግስገው የሚገኙ ጸረ ለውጥ ኃይሎችን የማጥራት" ተግባር ቀዳሚ ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።
በመንግስት በኩል የሚስተዋለው መለሳለስና ትዕግስት ልክ ሊበጅለት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለዜጎቿ የምትበቃና የምትመች አገር ሆና እያለች አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳና ግጭት ለመፍጠር በሚሰሩ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ ግድ ይላል ብለዋል ከቀድሞዎቹ የምክር ቤት አባላት መካከል አቶ አለማየሁ ደምሴ።
በርካታ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት በቀድሞው የ'ኢህአዴግ' መንግስት ብዙ ስቃይና እንግልት ይደርስባቸው እንደነበር አስታውሰው ''አሁን የተገኘውን ለውጥና ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር መደገፍ ያስፈልጋል'' ብለዋል።
አቶ ደረጄ ሃይሉና አቶ ስዩም ማሞ የተባሉት የቀድሞ ምክር ቤት አባላትም ሰላምና ጸጥታን ማስከበር ከምንም በላይ የመንግስት ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በተለይ በዚህ ወቅት አገሪቷን ለውስብስብ ችግሮች እየዳረጉ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የአገርን ህልውና መታደግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በተጨማሪም ገዢው ፓርቲ ለኢትዮጵያ አንድነት የሚሰሩ ኃይሎችን አንድ ላይ ማሳለፍና መሳተፍ እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የምክር ቤቱ አባላት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የህዳሴ ግድብን አስመልክተው ያስተላለፉትን የተሳሳተና ሃላፊነት የጎደለው መልእክትም አውግዘዋል።
ኢትዮጵያዊያን ግድቡን የተመለከተ የጋራ አቋማቸውን ለዓለም ማስተጋባታቸውን እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
"ለአገራችን ህልውና ሰላምና አንድነታችን በጋራ እንቁም" ሲሉም የቀድሞዎቹ የምክር ቤት አባላት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።