የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎችን ወደ አርሶ አደሩ ለማድረስ እየሰራሁ ነው -የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎችን ወደ አርሶ አደሩ ለማድረስ እየሰራሁ ነው -የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት
ሐዋሳ፣ ጥቅምት 23/2013 (ኢዜአ ) የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የስንዴ ዝርያዎችን ወደ አርሶ አደሩ በማድረስ ከውጭ የሚገባውን ምርት ለመተካት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
የወንዶገነት ግብርና ምርምር ማዕከል በምዕራብ አርሲ ዞን በነገሌ አርሲ ወረዳ በ40 ሄክታር ኩታገጠም የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ እያስተዋወቀ ያለውን የተሻሻለ የስንዴ ዝርያ ትላንት ለባለድርሻ አካላት በመስክ አሰጎብኝቷል ።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈቶ ኢስሞ በወቅቱ እንደገለጹት በኢትዮጵያ በባህላዊ ዘዴ ከሚመረተው ስንዴ የሚገኘው ምርት በሄክታር ከ25 ኩንታል አይበልጥም።
"በምርምር የተረጋገጡ የተሻሻሉ ዝርያዎች ወደ አርሶ አደሩ አለመድረስና ከማሳ ዝግጅት እስከ ምርት ስብሰባ ባለው ሂደት የተሻሻለ አሰራር ያለመከተል ለችግሩ ተጠቃሽ ምከንያቶች ናቸው" ብለዋል ።
በምርምር ማዕከላት ከ70 እስከ 80 ኩንታል ምርት የሚሰጡ የስንዴ ዝርያዎች መኖራቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ በሁለቱ መካከል ያለውን ክፍተት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።
ኢንስትቲዩቱ በስሩ በሚገኙ ከ20 በላይ የምርምር ማዕከላት ምርታማነትን ለማሻሻል የሚያስችሉ የምርምር ስራዎች እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ።
ሀገሪቱ ያቀደችውን በስንዴ ምርት ራስን የመቻል ዓላማ ለማሳካት በምርምር የተገኘውን ዘርና አመራረት ዘዴ ወደ አርሶ አደሩ ለማድረስ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል ።
የመስክ ምልከታው ለዚሁ አላማ መዘጋጀቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ከሰርቶ ማሳያ ማሳ የተገኘውን ልምድ ፈጥኖ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል።
የምርምር ማዕከላት ያላቸውን ቴክኖሎጂ ወደ አርሶ አደሩ ለማውረድ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አስገንዘበዋል ።
የወንዶገነት የግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ፊልጶስ በበኩላቸው በሀገሪቱ ባለፉት አስርት ዓመታት በስንዴ ምርታማነት ላይ መሻሻሎች ቢኖሩም እያደገ ከመጣው ፍላጎት አንጻር ከፍተኛ ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል፡፡
ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ የመሬት ዝግጅትና አስተራረስ፣ የዘር መረጣ፣ አዘራር፣ ክትትልና በሽታንና ተባይ ቁጥጥር ወሳኝ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በዘርፉ የሚስተዋሉ የዕውቀትና የተግባር ክፍተቶችን በምርምርና በቴክሎጂ ሽግግር በማረም ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት በሃገር ውስጥ ለመተካት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።
ስንዴን በክረምትና በመስኖ ለማልማት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር እየተሰራ ነው ብለዋል ።
"ማዕከሉ ለመስክ ምልከታ ያቀረበው ቃቃባ የተሰኘ የተሻሻለ የስንዴ ዝርያ ከ90 እስከ 115 ቀናት ውስጥ ለአጨዳ የሚደርስ መሆኑንም ገልጸዋል ።
"ማዕከሉ ለዕውቀት ሽግግር በመረጣቸውና ፈቃደኛ በሆኑ 47 አርሶ አደሮች ማሳ በምርጥ የስንዴ ዝርያው ላይ የሙከራ ልማት እየተካሄደ ነው" ያሉት ደግሞ የነገሌ አርሲ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የኤክስቴንሽን ማስፋፊያ ቡድን መሪ አቶ ጀማል መሐመድ ናቸው።
በኩታ ገጠም የአርሶ አደሮቹ ማሳ እየተካሄደ ያለው የስንዴ ልማት በሰብል ይዘቱ የተሻለ ውጤት የታየበት መሆኑን ጠቁመዋል ።
ከሙከራ ልማቱ የሚገኘውን ውጤት በወረዳው በሚገኙ 36 ቀበሌዎች ለማስፋፋት ከወዲሁ አቅጣጫ መያዙን ቡድን መሪው አስታውቀዋል።
ከመስክ ምልከታው ተሳታፊዎች መካከል አርሶ አደር ሶኮሬ ጉርሳ በኩታ ገጠም ማሳ እየለማ ያለው ስንዴ በይዘቱ ልዩና የተሻለ ሆኖ እንዳገኙት ገልጸዋል ።
የተሻሻለ አሰራር በመከተል የስንዴ ዝርያውን ለማልማት ማቀዳቸውን አመላክተዋል ።
ለስንዴ ሙከራ ልማቱ አንድ ሄክታር ማሳዬን በፈቃዴ ሰጥቻለሁ" ያሉት ደግሞ አርሶ አደር ተሽታ ገመቹ ናቸው።
ማዕከሉ በመስመር በመዝራትና በግብአት አጠቃቀም ጥሩ ግንዛቤ ያሰጨበጣቸው መሆኑን ተናግረዋል ።
ከዚህ ቀደም ከሚዘሩት ስንዴ በሄክታር እስከ 24 ኩንታል ምርት ያገኙ እንደ ነበር የገለጹት አርሶ አደሩ ዘንድሮ በማሳቸው ላይ እያለሙት ካለው የተሻሻለ የስንዴ ዝርያ ከ35 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቁ አመላክተዋል ።