ቀጥታ፡

አንድነታችንን በመጠበቅ ለህዳሴ ግድብ የምናደርገውን ድጋፍ እንቀጥላለን--የሐረር ከተማ ነዋሪዎች

ሐረር ጥቅምት 23 / 2013 (ኢዜአ) በአሁኑ ወቅት አንድነታችንን የበለጠ በመጠበቅ ለታለቁ የህዳሴ ግድብ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ያልተገባ ንግግርም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከሚያደርጉት ድጋፍ እንደማያግዳቸው ነው የገለጹት።

ነዋሪዎቹ  እንዳሉት ትራምፕ  በህዳሴ ግድብ ላይ የሰጡት አስተያየት  ከአንድ የሀገር መሪ የማይጠበቅና ተቀባይነት የሌለው ነው።

አቶ አብዱሰላም መሀመድ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ  ግድቡን በተመለከተ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት ድርድር እያደረጉ ባለበት ሁኔታ ትራምፕ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የሚጋፋና ሚዛናዊነት የጎደለው አስተያየት መስጠታቸው እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል።

የፕሬዚዳንቱ ሀላፊነት የጎደለው ንግግር ተቀባይነት  እንደሌላ ያገለጹት አስተያየተ ሰጪው በተለይ በአሁኑ ወቅት አንድነታችንን የበለጠ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ  ድጋፍ በማድረግ የደርሻቸው ሲወጡ መቆየታቸውን  ጠቁመው ኢትዮጵያዊያን እገዛቸውን ማጠናከር እንዳለባቸወም ተናግረዋል።

ግድቡ የጀመርነው በማንም ይሁንታ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያዊ ጥረትና ርብርብ ነው፤ አሁንም በማንም ትንኮሳ የግድቡ ግንባታ አይቆምም ያሉት ደግሞ ወይዘሪት ፍርዶሳ አቡበከር ናቸው ።

የፕሬዚዳንት ትራምፕ አድሎአዊ ንግግር ተቀባይነት እንደሌለውም ገልጸው ግድቡ ሀይማኖት፣ ዘር፣ የፖለቲካ ልዩነት ሳይለይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት ፕሮጀክት በመሆኑ  እንደጀመርነው ካለማንም ድጋፍ እንጨርሰዋለን  ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ፈጠነ በጅጋ የተባሉት አስተያየጥ ሰጪ በበኩላቸው የፕሬዚዳንቱ ንግግር  ከግል አስተያየት ያለፈ ትርጉም የሌለው ቢሆንም ሁላችንም አስቆጥቷል ብለዋል።

ታላቁ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን በመጠቀም ህዝቦቿን ከድህነት ለማውጣት እየተከናወነ ያለ ፕሮጀክት እንደሆነ ገልጸው  ሁሉም ዜጋ የጀመረውን ድጋፍ  መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል።

"በግሌም ታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት እንዲጠናቀቅ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ድጋፌን አጠናክራለሁ" ሲሉ አስታውቀዋል።

የፕሬዚዳንቱ ንግግር  ከአንድ የሀገር መሪ የማይጠበቅና ተገቢነት የሌለው ከመሆኑ ባለፈ በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ ትንኮሳ መሆኑን የተናገረው ደግሞ ወጣት ሰሚር ጆቴ ነው።

በሀገር ሉዓላዊነት እና በግድቡ ላይ የሚሰነዘር ማንኛውም ጥቃት ለመመከት እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

የፕሬዚደንቱ ንግግር  የግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ከመደገፍ እንደማያግዳቸው  የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ የጥፋት መልዕክታቸውን በመቃወም አውግዘዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም