ቀጥታ፡

በኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ባለው ማንነትን መሠረት ባደረገው ጥቃት አዝኛለሁ- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ ጥቅምት 23/2013 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በትላንትናው ምሽት በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ማንነትን መሠረት ባደረገው ጥቃት ማዘናቸውን ገለጹ::

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት የሃዘን መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

በኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ባለው ማንነትን መሠረት ባደረገው ጥቃት እጅግ ማዘኔን እገልጣለሁ።

የኢትዮጵያ ጠላቶች፤ "ወይ እኛ እንገዛለን፤ ወይ ሀገር አትኖርም" ብለው ተነሥተዋል። ለዚህም የጥፋት ዐቅማቸውን ሁሉ እየተጠቀሙ ነው። አንደኛው ዒላማቸውም የሕዝባችንን ቅስም መስበር ነው።

ለዚህ እየተጠቀሙበት ያለው ስልት ግራ ቀኝ የማያውቁ ሰዎችን እየሰበሰቡ በማሠልጠንና በማስታጠቅ በየአካባቢው ማንነትን መሠረት ያደረገ አረመኔያዊ ጥቃት ማድረስ ነው። ይህ ተግባር ሕዝቡ እንዲደናገጥ፣ እንዲፈራና በስሜት ያልተገባ ርምጃ እንዲወስድ የታለመ ነው።

መንግሥት በተለያዩ ቦታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ ያላቸውን ጥፋቶች በቅድሚያ መረጃ ሰብስቦ ርምጃ በመውሰድ ሲያከሽፍ ቆይቷል። ነገር ግን ያለፈው ሥርዓት ያወረሰንን ቀዳዳዎች ሁሉ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ደፍኖ መጨረስ አልተቻለም።

የጥፋት ኃይሎች ከውጭ ላኪዎቻቸውና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በሚገኙ ባልጠሩ አድር ባዮች ትብብር በሕዝባችን ላይ አሳዛኝ ጥቃት እያደረሱ ነው። ሁኔታው እንደ መሪም እንደ ዜጋም ልብ ይሰብራል።
ይህ ግን ከመንገዳችን ወደኋላ፣ ከግባችን ወደ ሌላ አያደርገንም። ተስፋ ቆርጠን እንድናቆም፣ ተሸንፈን እንድናፈገፍግ አያደርገንም። ከምንጊዜውም በላይ ኃይላችንን አሰባስበን እንድንነሣ ያደርገናል እንጂ።

መንግሥት ሁሉንም ዓይነት አማራጮች ተጠቅሞ የችግሩን ሰንኮፍ ይነቅለዋል። የጸጥታ አካላት ጥቃቱ ወደተፈጸመበት አካባቢ ተሠማርተዋል። ርምጃም እየወሰዱ ነው። በቀጣይም የሕዝባችንን ደኅንነት ለማስጠበቅ መንግሥት የመንግሥትነቱን ሥራ በቁርጥና በጽናት ይሠራል።

ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጸጥታ አካላት።፣ ምሁራንና ሌሎችም፧ መንግሥት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ የሚወስደውን ርምጃ በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም