ቀጥታ፡

አዲሱ የፖሊስ ዶክትሪን፣ ፖሊስ ትክክለኛ የህዝብ አገልጋይ እንዲሆን የሚያስችል ነው- ሰላም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23/2013 ( ኢዜአ) አዲሱ የፖሊስ ዶክትሪን፣ ፖሊስ ትክክለኛ የህዝብ አገልጋይ እንዲሆንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንዲችል የሚያደርግ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።

የፖሊስ ዶክትሪን ዝግጅት ሰብሳቢና በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በሶሻል ወርክና ሶሻል ዴቨሎፕመንት ተባባሪ ፕሮፌሰር ደመላሽ ካሳዬ ለኢዜአ እንዳሉት ዶክትሪኑ የፖሊስ ተቋማት ከፖለቲካ ተፅዕኖ ወጥተው ለሕብረተሰቡ ሰላምና ደህንነት እንዲሰሩ የሚያደርግ ነው።

ዶክትሪኑ በሀገሪቱ የፖሊስ ተቋምን በማዘመን የተሻሻለ የህዝብ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

በዋናነት ለዚህ ዶክትሪን ተግባራዊነት ደግሞ የሕብረተሰቡ ተሳትፎና ድጋፍ የጎላ እንደሆነ ነው የጠቀሱት።

ዶክትሪኑ ሲዘጋጅ በሀገሪቱ ሲሰራባቸው የቆዩ የዘርፉ ነባራዊ ሁኔታዎች በግብአትነት የተወሰዱ መሆኑንም አብራርተዋል።

ዶክትሪኑ በሰው ኃይል ልማት፣ የማዕረግ እድገት፣ የዕዝ ሰንሰለትን ጨምሮ ሌሎች ትግበራዎች ዘመናዊ እንዲሆኑ ያደርጋል ብለዋል ኮማንደር ደመላሽ።

የፖሊስ  አገልግሎት በሙያ ብቻ እየተመራ ለማህበረሰቡ ፈጣንና ውጤታማ አገልግሎት መስጠት መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም ዶክትሪኑ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

ፖሊስ ከሕብረተሰቡ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ማድረግ የሚችልበት የተሻለ አሰራር የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይም ማሕበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት (ኮሚዩኒቲ ፖሊሲንግን) ማዘመንና ማጠናከር የሚያስችል አሰራር የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል።

በሰላም ሚኒስቴር የሕግ ማስከበርና ወንጀል ቁጥጥር ዳይሬክተር ጀነራል ምክትል ኮሚሸነር ጋሹ አለማየሁ እንዳሉት ዶክትሪኑ የፖሊስ ተቋምን በማዘመን ህዝባዊ አገልግሎትን የሚያጠናክር ይሆናል።

የፖሊስና ህብረተሰቡን ትብብርና ቅንጅታዊ አሰራር ለማሳለጥም ዶክትሪኑ ምቹ መሆኑን ገልጸዋል።

የፖሊስን ገለልተኝነት፣ የስነ-ምግባርና የምልመላ ስርአት ለማስተካከልም አዲሱ የፖሊስ ዶክትሪን መፍትሄ መሆኑን ምክትል ኮሚሸነሩ ገልጸዋል።

በአዲሱ የፖሊስ ዶክትሪን የፖሊስ ተቋም ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ነፃ ሆኖ ህዝብን በእኩልነት የማገልገል ሃላፊነት ያስቀምጣል።

የፖሊስ ዶክትሪኑ ከመስከረም 28 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም