የአንበጣ መንጋ በ111 ሄክታር የሰብል ማሳ ላይ ጉዳት አደረሰ - ኢዜአ አማርኛ
የአንበጣ መንጋ በ111 ሄክታር የሰብል ማሳ ላይ ጉዳት አደረሰ
ሰቆጣ/አክሱም ጥቅምት 23/13 (ኢዜአ) በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የተከሰተ የአንበጣ መንጋ በ111 ሄክታር ማሳ የሚገኝ ሰብል ላይ ጉዳት በማድረሱን የአስተዳደሩ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በሌላ በኩል የአክሱም ዩኒቨርሲቲ በትግራይ የአንበጣ መከላከል ስራን እያገዘ መሆኑ ተነግሯል ።
የዋግ ህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ደስታየ ጌታሁን ለኢዜአ እንደገለፁት በብሄረሰብ አስተዳደሩ ከጥቅምት 10 ቀን 2013 ዓም ጀምሮ የአንበጣ መንጋ ተከስቷል ።
የአንበጣ መንጋው በአበርገሌ፣ ፃግብጅና ሰቆጣ ዙሪያ ወረዳዎች በመስፋፋት በ111 ሄክታር ማሳ ላይ የሚገኝ የማሽላና ሰሊጥ ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል ።
ከክልሉ በተገኘ ድጋፍ ኬሚካል በመርጨት አንበጣውን ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ከአንበጣ መንጋ መከላከል ጎን ለጎን የመንግስት ሰራተኞች ፣ የጸጥታ አካላትና ተማሪዎችን በማስተባበር የደረሱ ሰብሎች እንዲሰበስቡ እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል ።
በሌላ በኩል የአክሱም ዩኒቨርሲቲ በትግራይ ክልል የአንበጣ መንጋ ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥረት እየደገፈ መሆኑ ተመልክቷል ።
የዩኒቨርሲቲው የአንበጣ መከላከል ግብረ ኃይል አስተባባሪ ዶክተር ታደሰ ደስታ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የአንበጣ መንጋ ከተከሰተ አንስቶ ዩኒቨርሲቲው ድጋፉን አላቋረጠም።
መንጋው በተከሰተባቸው የክልሉ ወረዳዎች የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በመገኘት የመከላከል ስራውን እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል ።
የአንበጣ መንጋውን ከመከላከል ጎን ለጎን የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
ዩየኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ከደሞዛቸው ላይ 253 ሺህ ብር በማዋጣት ለአንበጣ መንጋ መከላከል ስራ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል ።
ዩኒቨርሲቲውም በተቋም ደረጃ 500 ሺህ ብር መድቦ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል ።
እስካሁንም 40 የኬሚካል መርጫ መሳሪያዎች፣ 450 ማጭዶችና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጋቸውን አስተባባሪው አስታውቀዋል ።