የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሀኪሞች ተመረቁ

99
አዲስ አበባ ግንቦት 3/2010 የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠናቸውን ሰባት የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሀኪሞች አስመረቀ። ኮሌጁ ለሁለት ዓመት ተኩል ያሰለጠናቸውን አራት የኩላሊት ንቅለ ተከላ ስፔሻሊስቶችና ሶስት የኩላሊት እጥበት የሚሰሩ ሀኪሞችን ነው ያስመረቀው። በሆስፒታሉ የአካዳሚክስና ምርምር ምክትል ፕሮቮስት ዶክተር ባልካቸው ንጋቱ ስልጠናው በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ በመጡ ሀኪሞች በሆስፒታሉ የተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል። ህክምናው እስካሁን ከውጭ በመጡ ሀኪሞች እገዛ ሲሰጥ እንደነበረና የሀኪሞቹ መመረቅ ከአሁን በኋላ ህክምናውን በኢትዮጵያውያን ሀኪሞች ብቻ መስጠት እንደሚቻል ያሳየ ነው ብለዋል። በሌሎች ዘርፎችም የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስቶችን በኢትዮጵያ ማሰልጠን እንደሚቻል፤ በኢትዮጵያውያን ብቻ መስጠት እንደሚቻልም ማሳየት የሚችል መሆኑን ተናግረዋል። በዘርፉ ስፔሻሊስት ሀኪሞችን የማፍራት ሂደቱ እንደሚቀጥል ገልፀው ከዚህ በተጨማሪም ለኩላሊት ህክምና ብቻ የሚሰሩ ነርሶችን በማስተርስ ፕሮግራም ለማሰልጠን የትምህርት መርሃ-ግብር የተቀረጸ ሲሆን፤ ከአራት ወራት በኋላም ይጀመራል ብለዋል። በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን ሆስፒታሉ ቀደም ሲል 81 የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ማድረጉንና 94 በመቶው ስኬታማ እንደነበር ገልጸዋል። በዚህም ካደጉ አገራት ሆስፒታሎች ጋር ተመሳሳይ ብቃት ላይ እንደሚገኝ ነው ያመለከቱት። በአገሪቱ በ11 ሆስፒታሎች የኩላሊት እጥበት ህክምና እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው ሚኒስቴሩ ቀስ በቀስ የንቅለ ተከላ ህክምናን ወደ ሌሎች ሆስፒታሎች ለማስፋፋት እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል። በሆስፒታሉ የኩላሊት ህክምና የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አስተዋፅኦ ላደረጉ መምህራንና አመራሮች በስነ-ስርዓቱ ላይ ዕውቅና ተሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም