በዓባይ ጉዳይ አንዱ ጠያቂ ሌላው ተጠያቂ ሊሆን አይገባም - ፖለቲከኞች - ኢዜአ አማርኛ
በዓባይ ጉዳይ አንዱ ጠያቂ ሌላው ተጠያቂ ሊሆን አይገባም - ፖለቲከኞች
አዲስ አበባ ጥቅምት 23/2013 (ኢዜአ) በዓባይ ጉዳይ አንዱ ጠያቂ ሌላው ተጠያቂ መሆን አይገባም ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ተናገሩ።
ከኃያላን መሪዎች ወሬ ይልቅ ለውስጣዊ አገራዊ አንድነትና ለዲፕሎማሲው መስክ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች እንደሚሉት ዓባይ በፖለቲካዊ ርዕዮትም ሆነ በሌላ የልዩነት መንገድ ኢትዮጵያዊያንን የሚለያይ ሳይሆን ወደ አንድ የሚያመጣ ፕሮጀክት ነው።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረ "በዓባይ ጉዳይ አንዱ ጠያቂ፤ ሌላው ተጠያቂ መሆን አይገባም" ይላሉ።
'የተጀመረውን ግድብ መጨረስ ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ነው' ያሉት አቶ ማሙሸት ፓርቲያቸው ለዚህ የሚቻለውን ድጋፍ እንደሚያደርግ፣ ደጋፊዎቹንና ሕዝቡን በመቀስቀስም ግድቡ ከግብ እንዲደርስ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያዊያን ወደ አንድ በመምጣት በዕውቀት፣ በገንዘብና በቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ሊተባበሩ እንደሚገባም ተናግረዋል።
እንደ ዶናልድ ትራምፕ ያሉ መሪዎችን ንግግር ለፕሮፓጋንዳ ማዋል ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸው፤ ለውስጣዊ አገራዊ አንድነት ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም ነው አቶ ማሙሸት የተናገሩት።
የአቶ ማሙሸትን ሃሳብ የሚጋሩት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናም በአገር አንድነት ላይ ከንግግር የዘለለ ተጨባጭ ስራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
ለዓባይም ሆነ ለሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ዕውን መሆን በቅድሚያ የውስጥ መግባባት ሊኖር እንደሚገባም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ /ኢዜማ/ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ በበኩላችው ኢትዮጵያ እንደ ማንኛውም ሉዓላዊ አገር ተፈጥሯዊ ሀብቷን አልምታ የመጠቀም መብት እንዳላት ይናገራሉ።
ምንም ይሁን ምን፤ አንድ አገር በሌላ አገር ላይ ተጽዕኖ ማድረግ እንደማይገባ ገልጸው፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ በዲፕሎማሲው መስክ ጠንካራ ስራ እንደሚሻ ተናግረዋል።