የኢትዮጵያ መንግስት ለደቡብ ሱዳን ሐኪሞች የትምህርት ዕድል ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መንግስት ለደቡብ ሱዳን ሐኪሞች የትምህርት ዕድል ሰጠ
ጥቅምት 23/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንግስት ለ100 የደቡብ ሱዳን ሐኪሞች የትምህርት ዕድል መስጠቱን የሱዳን ፖስት ዘገባ አመለከተ።
ይህን ያሉት የደቡብ ሱዳን ጤና ሚኒስቴር የስልጠናና የሙያ ልማት ጀኔራል ዳይሬክተር ዶክተር ማይክል ማዲንግ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫቸው ነው።
በዚህም የኢትዮጵያ መንግስት የሰጠውን የትምህርት ዕድል ለመጠቀም ከዚህ ሳምንት መጀመሪያ ጀምሮ ፍላጎት ያላቸው ሐኪሞች መመዝገብ ይችላሉ ብለዋል።
"ስፔሻላይዝ ማድረግ ለሚችሉ ሐኪሞች የጤና ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ መንግስት የትምህርት ዕድል ማግኘት ችሏል" ሲሉ ተናግረዋል።
ፍላጎቱ ያላቸው ሐኪሞች ተመዝግበው መወዳደር እንደሚችሉ ገልጸው፤ የሚመዘገቡ ሐኪሞች የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን የሚቀርብላቸውን የመግቢያ ፈተና ማለፍ ስለሚጠበቅባቸው መዘጋጀት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የፈተና ሂደቱን የሚመሩት ከኢትዮጵያ የሚሔዱ ሐኪሞች ቡድን አባላት እንደሚሆኑም ጠቁመዋል።
የደቡብ ሱዳን ጤና ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዶክተር ቱኡ ሎይ በበኩላቸው የዕድሉ ተጠቃሚ የሚሆኑት የመግቢያ ፈተናውን ማለፍ የሚችሉ ሐኪሞች ብቻ እንደሆኑ አስገንዝበዋል።
በመሆኑም በዕድሉ ለመጠቀም የሚመዘገቡ ሐኪሞች ለፈተናው በቂ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።