ቀጥታ፡

ማህበሩ ለሁለት ሆስፒታሎች ለሕክምና አገልግሎት መስጫ የሚውሉ ቁሶችን ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ ጥቅምት 22/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በምዕራብ ሸዋ ዞን ለሚገኙ ሁለት ሆስፒታሎች ከ850 ሺህ ብር ባላይ ግምት ያላቸውና ለሕክምና አገልግሎት መስጫ የሚውሉ ቁሶችን ድጋፍ አደረገ።

ማህበሩ ከኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፉ ጋር በመሆን ዛሬ ድጋፍ ያደረገው በምዕራብ ሸዋ ዞን ለሚገኙ ጌዶ እና ባኮ ሆስፒታሎች ነው።

በእዚህም ማህበሩ ለእያንዳንዳቸው10 ሺህ ሌትር ውሃ የሚይዝ ሮቶ፣ ፍራሾች፣ ብርድልብሶች፣ የንህጽና መጠበቂያ ሳኒታዘር፣ የአፍንና አንፍጫ መሸፈኛ ጭብሎችና ሌሎች መሰል ድጋፎችን አድርጓል።

የማህበሩ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ የቦርድ አባል አቶ ዳውድ ሙሜ በእዚህ ወቅት እንዳሉት ማህበሩ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሰው ሰራሽኝና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲደርሱ ቀድሞ በመድረስ ሰብአዊ ድጋፍ ያደርጋል።

በዛሬው ዕለት የተደረገው ድጋፍ ሆስፒታሎቹ ያሉባቸውን ችግሮች በተወሰነ መልኩ ለማቀላል እንደሚረዳም ነው የገለጹት።

በአሁኑ ወቅት ማህበሩ ለሚከሰቱ የተለያዩ አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ ዳውድ፣ ህብረተሰቡም ማህበሩ የበለጠ እንዲጠናከር አባል በመሆንና በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አመልክተዋል።

የኮሮናቫይረስ በአገሪቱ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ማህበሩ በክልሉ 115 ሺህ በጎ ፍቃደኞችን በማሰማራት የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የተለያዩ ድጋፎችን እንዳደረገም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የአስተዳደር ቦርድ አባል አቶ ኢያሱ ኩምሳ በበኩላቸው በአገሪቱ የተለያዩ አደጋዎች ሲከሰቱ ማህበሩ ከሚያደርጋቸው የተለያዩ ሰብዓዊ ድጋፎች በተጨማሪ የተለያዩ ህዝባዊ ተቋማትን በመደጋፍ ለህብረተሰቡ የተሳለጠ አገልግሎት እንዲሰጡ በማገዝ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

እነደ አቶ ኢያሱ ገለጻ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በሰብል ላይ ባደረሰው ጉዳት አርሶአደሩ እንዳይጎዳ ማህበሩ የተለያዩ ተቋማትና በጎፍቃደኞችን በማስተባበር ድጋፍ ላመድርግ እየሰራ ይገኛል።

ድጋፍ የተደረገላቸው የሆስፒታሎቹ ሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው ማህበሩ ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ድጋፉ ያላባቸውን ችግር እንደሚያቃልላቸው ተናግረዋል።

"ሆስፒታሉ ከ80 ሺህ ባላይ ለሚሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም  ታካሚዎች የሚለብሱት ብርድልብስ እና የፍራሽ እጥረት ነበረበት፤ ድጋፉ ይሄን ችግር ያቃልልናል።" ያሉት ደግሞ  የጌዶ አጠቃላይ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር መስፍን ተሾመ ናቸው።

የባኮ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ ሽብሩ በበኩላቸው ድርጅቱ ያደረገላቸው ድጋፍ በሆስፒታሉ ለሚሰጠው የአስተኝቶ ህክምና ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው ለሆስፒታሉ የተደረገው ድጋፍ በሆስፒታሉ የተሻለ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት እንደሚረዳቸው ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በሆስፒታሉ ለመገልገል ሲሄዱ ከቁሳቁስ እጥረት ጋር በተያያዘ የሚያገጥሙ ችግሮችን ይፈታል ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡት  የአካባቢው ነዋሪ አቶ ገነቲ በርኪ ናቸው።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም