ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በቀጣይ 30 ዓመታት የሚኖራትን የህዝብ ቁጥር እድገት በልማት ዕቅዷ ማጤን ይኖርባታል---ምሁራን

አዲስ አበባ ጥቅምት 22/2020 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 30 ዓመታት የሚኖራትን የህዝብ ቁጥር እድገት በምትቀርጻቸው የልማት ዕቅዶች ታሳቢ እንድታደርግ ምሁራን መከሩ። 

"ባለሰማያዊ አርማ የተሰኘ" የኢትዮጵያን 2050 ተግዳሮቶችና እድሎችን የሚዳስስ ሪፖርትን አስመልክቶ በበይነ መረብ በመታገዝ መግለጫ ተሰጥቷል።

ሪፖርቱ በአገር ውስጥና በውጪ በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን የተዘጋጀ ሲሆን በከተማ ልማት፣ ኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ፣ ግብርና፣ ስነ-ህዝብ፣ ምጣኔ ሃብትና ሌሎች የሙያ ዘርፎች ላይ ያተኮረ ነው።

በአገር ውስጥና በተለያዩ የዓለም አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ታህሳስ 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ባደረጉት ጉባኤ ላይ የቀረቡ ጥናታዊ ጹህፎችና አስተያየቶችንም አጠቃሎ መያዙ ተመላክቷል።

ፈጣን የከተሞችና የምጣኔ ሃብት እድገት፣ የጾታ እኩልነትን ጨምሮ አሥር የትኩረት አቅጣጫዎች እንዲሁም አምስት ዋና ዋና የእስትራቴጂ እርምጃዎችን ሪፖርቱ ማካተቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያን እድገትና ልማት በተመለከተ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው የህዝብ ብዛትና የማህበራዊ ምጣኔ ሃብት ክንውን ውጤት አለመመጣጠን የሪፖርቱ ዋና ማጠንጠኛ መሆኑም ነው የተመላከተው።

በመግለጫው የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር በቀጣዮቹ ሦስት አስርት ዓመታት 200 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ሪፖርቱ ግምት ማስቀመጡም ተገልጿል።

በእዚህም የሚቀረጹ የልማት ዕቅዶች ይህን የህዝብ ቁጥር እድገት ታሳቢ ማድረገ እንዳለባቸው ምሁራኑ መክረዋል።

በሪፖርቱ የህዝብ እድገት በምጣኔ ሃብት እድገት ላይ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከህዝብ ዕድሜ ስብጥር ጋር ተያይዞ ቀርቧል።

በእዚህም የኢትዮጵያ የዕድሜ ስብጥር እስከ 14 ዓመት ያለው እየቀነሰ መምጣቱን የገለጸው ሪፖርቱ፣ ከ15 እስከ 64 ዓመት እየጨመረ መሆኑን አመላክቷል።

በአሁኑ ወቅት ሥራ መስራት የሚችለው የህብረተሰብ ክፍል 50 በመቶ ሲገመት ከ30 አመት በኋላ 63 በመቶ ሊደርስት እንደሚችል ተቀምጧል።

ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት መስጠት፣ ለወጣቱ የሥራ ዕድል መፍጠርና የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ ከተቻለ የህዝብ ቁጥር ለዕድገት መልካም አጋጣሚ ይሆናል ተብሏል።

ኢትዮጵያ አሁን እያዘጋጀት ያለውን የ10 ዓመት ዕቅድ ጨምሮ ለረዥም ጊዜ የምታወጣቸው የልማት እቅዶች ለአምራች ኃይሉ የሥራ እድል ሊፈጥሩ የሚችሉ መሆን እንዳለባቸው ምሁራኑ መጠቆማቸውን ሪፖርቱ አስቀምጧል።

ከማህበራዊ፣ ከምጣኔ ሃብት፡ ከጂኦ-ፖለቲክስና ሌሎች ክስተቶች ጋር ማጣመር በአገሪቱ የወደፊት የእድገት አቅጣጫና ውጤት ላይ ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝቧል።

ሪፖርቱ በምግብ ዋስትና፣ በንጹህ የመጠጥ ውሃ እና በአስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲሁም በትራንስፖርት መሰረተ ልማትና በሌሎች ዘርፎች ያሉ መሰረታዊ ተግዳሮቶችንም አስቀምጧል።

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የግብርናን ምርታማነት ማሳደግና በዘመናዊ አሰራር መደገፍ እንደሚገባ በመፍትሄነት አመላክቷል።

በገጠር አካባቢ በተለያዩ የምጣኔ ሃብት ቀጠናዎች የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብት ውጤታማ በሆነ ዘዴ ለሁለገብ ልማት ማዋል እንደሚቻልም መክሯል።

ሪፖርቱ በቀጣይ የተለያዩ ውይይቶች የሚደረጉበት ሲሆን ፖሊሲ አውጪወችና ውሳኔ ሰጪ አካላት በግበአትነት ይጠቀሙበታል ተብሏል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ በበይነ መረብ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያዊያን ምሁራን በራሳቸው ተነሳሽነት ለአገራቸው እድገት አስተዋጽኦ ለማድረግ ሪፖርቱን በማዘጋጀታቸው አመስግነዋል።

መንግስት ሪፖርቱን በጥንቃቄ በማየት በቀጣይ ለሚከናወኑ የልማት ዕቅዶች በግብአትነት እንደሚጠቀምበት ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ 2050 ተግዳሮቶችና እድሎች ማህበር ሊቀመንበር ኢንጂነር ተስፋዬ ወርቅነህ ሪፖርቱ መንግስት የሚያቅዳቸው የ10 እና የ20 ዓመት ዕቅዶች ከህዝብ ቁጥር ጋር ተጣጥመው እንዲታዩና ችግሮችን ከነመፍትሄዎቻቸው ያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል።

ማህበሩ ኢትዮጵያ በምታከናውናቸው የልማት ሥራዎች ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግና ቀጣይ አካሄዶችን ለማመላከት በምሁራን ስብስብ የተደራጀ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም