አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ለሕዳሴው ግድብ 300 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ለሕዳሴው ግድብ 300 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ እየሰራ ነው
አዲስ አበባ ጥቅምት 22/2013 (ኢዜአ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 300 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አስታወቀ።
የሕዳሴው ግድብ ዋንጫ ርክክብ ሥነስርአት በክፍለ ከተማው ተካሂዷል፡፡
በክፍለ ከተማው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ሸዋንግዛው አበበ የግድቡ ዋንጫ በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች ሲዘዋወር መቆየቱን አስታውሰዋል።
ዋንጫው ከኮልፌ ክፍለ ከተማ ወደ አዲስ ክፍለ ከተማ ከመምጣቱ በፊት የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑ እንደነበረም ተናግረዋል፡፡
በክፍለ ከተማው ከጥቅምት 14 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በተከናወኑ ሥራዎች ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከ188 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዢና በስጦታ መሰብሰቡን ጠቁመዋል፡፡
"ዋንጫው ከዛሬ ጀምሮ በክፍለ ከተማው በሚኖረው የ15 ቀናት ቆይታም ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ ከክፍለ ከተሞች የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ይሰራል" ብለዋል፡፡
"በተለይ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ያለበት በመሆኑ በዕቅድ የተያዘውን ለማሳካት ይቻላል" ሲሉም ዶክተር ሸዋንግዛው ገልጸዋል፡፡
ህብረተሰቡ በውጭ ኃይሎች የሚሰነዘሩ ያልተገቡ አስተያየቶችን ወደ ጎን በመተው ለሕዳሴው ግድብ የሚያደርገውን ድጋፍና አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
በተለይ በቅርቡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግድቡን አስመልክቶ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ያስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያዊያንን ከማስቆጣት ባለፈ ቁጭት የፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዋንጫ ርክክብ ስነስርአቱ ላይ የተገኙት የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ይታያል ደጀኔ በበኩላቸው የሕዳሴው ግድብ የተጀመረበት እለት ታሪካዊ ቀን መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የግድቡ ግንባታ እውን ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ ድምጽና በአንድ ልብ አብሮ በመቆም ለግድቡ ያላሰለሰ ድጋፍ ማድረጉንና አሁንም እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያን ህዝብ በአንድነት ያስተሳሰረ የልማት ውጥን መሆኑን ጠቁመው፣ ግድቡ በኢትዮጵያ ውስጥ ልማትን ለማፋጠንና ድህነትን ለማጥፋት በሚደረገው እንቅስቃሴ የሚኖረው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
"የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማም ነዋሪ ለዚህ የልማት ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እየሰጠ ይገኛል" ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ህብረተሰቡ ለውስጥም ሆነ ለውጭ አፍራሽ ኃይሎች ጆሮ ባለመስጠት ልማቱን እያጠናከረ መሆኑን አመልክተዋል።
በዝግጅቱ ላይ ከአዲስ ከተማ ክፍለከተማ አሥር ወረዳዎች የተውጣጡ ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን በክፍለ ከተማው የወረዳ ሦስት አስተዳደር የመጀመሪያውን የሀብት አሰባሰብ ሂደት ለማከናወን ዛሬ የሕዳሴ ዋንጫውን ተረክቧል፡፡
የፖሊስ ማርሽ ባንድና የክፍለ ከተማው የኪነት ቡድን የተለያዩ ጥዑመ ዜማዎችን በማቅረብ ለዝግጅቱን ድምቀት ሰጥተውታል፡፡