ከተሞች የራሳቸው ጸጋ ቢኖራቸውም በጸጋቸው ልክ ገዝፈው እየታዩ አይደለም ...ኢንጂነር አይሻ መሐመድ - ኢዜአ አማርኛ
ከተሞች የራሳቸው ጸጋ ቢኖራቸውም በጸጋቸው ልክ ገዝፈው እየታዩ አይደለም ...ኢንጂነር አይሻ መሐመድ
አዲስ አበባ ጥቅምት 22/2013 (ኢዜአ) በከተሞች የብልጽግና ማረጋገጫ ጸጋዎች ቢኖሩም ከተሞች ባላቸው ጸጋ ልክ ገዝፈው የሚታዩ እንዳልሆኑ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ተናገሩ።
በአሁኑ ወቅት በከተሞች እየገጠሙ ያሉ ችግሮች ኢትዮጵያን የማይመጥኑና ካሏት እሴቶች ጋርም የሚቃረኑ መሆናቸውም ተመልክቷል።
በዓለም ለ7ኛ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ "የተሻለ ከተማ ለተሻለ ሕይወት" በሚል መሪ ቃል የተከበረውን የዓለም የከተሞች ቀን አስመልክቶ "ጥቅምት የከተሞች ወር" በሚል ሲከናወኑ የነበሩ መርሃ ግብሮች ማጠቃለያ ስነ ስርዓት ትናንት ማምሻውን በአንድነት ፓርክ ተካሄዷል።
በማጠቃለያ ስነ ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ከተማና የከተማ ሕይወት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውንና አንዱን ከአንዱ ነጥሎ ማየት እንደማይቻል ተናግረዋል።
የከተሞች ድክመትም ሆነ ጥንካሬ በከተሞቹ ውስጥ የሚኖረው ማህበረሰብ መገለጫ እንደሆኑና ካለው ሕይወት ጋር የሚቆራኙ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት ከተሞችን እየገጠሙ ያሉ ችግሮች ኢትዮጵያ ካሏት እሴቶች ጋር የሚቃረኑና የማይመጥኑ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።
ከተሞቻችን ያላቸውን የተዘበራረቀ ምስል ወጥነት ወዳለው የከተሞች መልክ ለመቀየር በሚደረገው አገራዊ ጉዞ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም ገልጸዋል።
"በከተሞቻችን ውስጥ ተፈጥሮና ሰው የሚባሉ የብልጽግና ማረጋገጫ ጸጋዎች ቢኖሩም ከተሞች ባላቸው ጸጋ ልክ ገዝፈው የሚታዩ አይደሉም" ብለዋል ኢንጂነር አይሻ።
"ሩቅ አልመን ከከፍታው እንድንወጣ የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል" ያሉት ሚኒስትሯ፣ ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያ መሬት ሁሉ የሚከብሩባትና የሚንግሱባት ከተማ ለመስራት የጋራ ትብብር አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከተሞችን የሚያስተዳድሩ አመራሮች የሚመሯቸውን ከተሞች ገጽታ ለመቀየር በትኩረት መስራት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
ኢንጂነር አይሻ እንዳሉት፣ ከተሞች የምርታማነትና የብልጽግና ማዕከላት እንዲሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ አዘጋጅቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።
የከተሞች ድክመት የኢትዮጵያ ድክመት፤ የከተሞች ስኬት የኢትዮጵያ ስኬት እንደሆነ ገልጸው፣ "ከተሞች እርስ በእርስ በመተጋገዝና በጋራ በመስራት ለከተሞች ብልጽግና መትጋት ይገባቸዋል" ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው የከተሞችን እድገት ለማረጋገጥ ለህዝብ ቅርብ መሆንና ችግሮችን ፈጥኖ መፍታት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ከተሞች በቀጣይ ለመልካም አስተዳደር፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም አመልክተዋል።
"የተመሰረተው የኢትዮጵያ ከንቲባዎች ፎረም ከንቲባዎች ስለ ከተሞች ብልጽግናና ስለ ሰላም የምንመክርበት፣ እርስ በእርስ ትስስር የምንፈጥርበትና ልምድ የምንለዋወጥበት መድረክ ይሆናል ብለዋል።
ትናንት በተካሄደው በ"ጥቅምት የከተሞች ወር" የማጠቃለያ መርሃ ግብር በገለልተኛ መዛኝ ተቋማት ምዝና በከተሞች የማስፈጸም አቅም፣ በመሰረት ልማት፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በጾታ እኩልነትና የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ዘርፎች የተሻለ ውጤት ያመጡ ከተሞች ተሸላሚ ሆነዋል።
በሁሉም ዘርፎች አጠቃላይ አሸናፊ የሆነው ወልዲያ ከተማ ሲሆን ጎንደር እና ሰቆጣ ከተሞች በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሦስተኛ በመውጣት ተሸልመዋል።
ለከተሞች እድገት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትም እውቅና ተሰጥቷል።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተዘጋጀውን ሽልማት ለተሸላሚዎች አበርክተዋል።
በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የከተማ ከንቲባዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም ተገኝተዋል።
"ጥቅምት የከተሞች ወር" መርሃ ግብር ጅማሮውን በደቡብ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ አድርጎ በአዲስ አበባ በተከናወኑ ዝግጅቶች ፍጻሜውን አግኝቷል።
በአዲስ አበባ በነበረው ዝግጅት የኢትዮጵያ ከንቲቦች ፎረም የተመሰረተ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የፎረሙ ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸውም የሚታወስ ነው።