ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል የ61 ሴክተር መስሪያ ቤቶች ሰራተኞች ለገበታ ሀገር የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ

ጋምቤላ፣ ጥቅምት 21/2013 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የ61 የመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች ሰራተኞች ለገበታ ለሀገር ልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ከአንድ ወር ደመወዛቸው እስከ 50 በመቶ መለገሳቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤታ አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ኡዶል አግዋ ለኢዜአ እንደገለጹት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለታቀዱት ሶስት የገበታ ለሀገር የልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ በክልሉ የተጀመረው የሀብት ማሰባሰብ መረሃ ግብር ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ቀደም ሲል ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች ከመስከረም ወር ጀምሮ የሚከፈል የአንድ ወር ሙሉ ደመወዛቸውን መለገሳቸውን አስታውሰዋል ።

በአሁኑ ወቅትም 61 የክልል ሴክተር መስሪያ ቤቶች ሰራተኞች ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ከአንድ ወር ደመወዛቸው ላይ ከ25 እስከ 50 ከመቶ መለገሳቸውን ተናግረዋል።

ሰራተኞች የለገሱት ገንዘብም ከተያዘውና ቀጣይ ህዳር ወር ጀምሮ በስድስት ወራት ጊዜ የሚከፈል መሆኑንም ገልጸዋል።

በክልል ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተጀመረው የሃብት ማሰባሰብ መረሃ ግብር በዞንና በወረዳ የመንግስት ሰራተኞች እየተካሄደ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በቀጣይም በክልሉ የሚገኙ ባለሃብቶችንና የንግዱን ማህበረሰብ በማወያየትም ተመሳሳይ የሀብት ማሰባሰብ ስራ እንደሚከናወንም አቶ ኡዶል አስታውቀዋል።

“የታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ በመሰል ፕሮጀክቶች ህዝቡ እንዲሳታፍ መደረጉ የባለቤትነት ስሜትን የሚፍጠር ከመሆኑም ባለፈ ሌሎች ተመሳሳይ የልማት ፕሮጀክቶችን የማከናወን ባህልን ያሳድጋል” ብለዋል።

የክልሉ ዳያስፖራ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኦኬሎ ኮም በሰጡት አስተያየት ፕሮጀክቶቹ ለትውልድ የሚተላለፉና ለዜጎችም የስራ እድል የሚፈጥሩ በመሆናቸው የአንድ ወር ሙሉ ደመወዛቸውን መለገሳቸውን ተናግረዋል። 

ፕሮጀክቶቹ የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ በቱሪዝም ልማት ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ስለሚፈጥሩ ከአንድ ወር ደመዛቸው ላይ 50 ከመቶ መለገሳቸው የገለጹልን ደግሞ የክልሉ መስተዳዳድር ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አዲሱ መታፊያ ናችው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም