የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ማሳደግ ለሰላምና ለአንድነት የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ቱሪዝም ኢትዮጵያ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ማሳደግ ለሰላምና ለአንድነት የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ቱሪዝም ኢትዮጵያ ገለጸ
አክሱም ጥቅምት 21/2013 (ኢዜአ) የሀገር ውስጥ የቱሪዝም እንቅስቃሴ የሰዎችን ሰላማዊ ግንኙነትና ትስስር በማሳደግ ለሀገር አንድነትና ሰላም የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ቱሪዝም ኢትዮጵያ አስታወቀ።
ቱሪዝም ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለጎብኚዎች ክፍት ለማድረግ ለዘርፉ ተዋናዮች በአክሱም ከተማ ስልጠና ሰጥቷል።
የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ቱሪዝም ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና ማህበረሰባዊ ትስስር ያጠናክራል።
የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ማጠናከር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ከመሆኑም በተጨማሪ ሰላም ለመፍጠር ትልቅ ሚና እንዳለው አቶ ሰለሺ ተናግረዋል።
''ቱሪዝም ኢኮኖሚን ያንቀሳቅሳል፣ ማህበራዊ ግንኙነት ያሰፋል፣ ሰላምና አንድነትን ያጠናክራል'' ብለዋል።
ሀገራዊ መዋቀር እና ስትራተጂ ባለመኖሩ የሀገር ውስጥ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዳላደገ የገለጹት አቶ ስለሺ፤ "አሁን ሀገር አቀፍ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንቅስቃሴ ስትራተጂ ተቀርጾ ስራው በመጀመሩ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ይረዳል" ብለዋል።
ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም የሰው ሃይል እና ፋይናንስ እንደሚመደብለት ጠቅሰው፤ ሀገርን ቀድሞ የማወቅ ባህልን ለማሳደግ የሀገርህን እንወቅ ክበባት በትምህርት ቤቶች፣ በመንግስትና በግል ተቋማት ተጠናክረው እንዲቀሳቀሱ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ቱሪዝም ከፖለቲካ ተነጥሎ መታየት እንዳለበት የተናገሩት አቶ ስለሺ፤ "ዘርፉ የሰዎችን ግንኙነትና ትስስር በማጎልበት የተረጋጋ ፖለቲካ እንዲኖር ለማድረግ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው መገንዘብ ይግባል" ብለዋል።
የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ማሳደግ ከሀገር አልፎ ለአለም ማህበረሰብ የሚተርፍና የኢትዮጵያን ገጽታ የሚያስተዋውቅ መሆኑንም ገልጸዋል።
በቱሪዝም ኢትዮጵያ በአገሪቷ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን የማልማት፣ ታሪካዊ እና የተፈጥሮ መስህቦች ለኢትዮጵያውያን እና ለአለም ማህበረሰብ የማስተዋወቅ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ቱሪዝም እና አርኪዮሎጂ ኢንስቲዩቲት ዳይሬክተር አቶ ተክለብርሃን ለገሰ በበኩላቸው የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንቅስቃሴን ማበረታታት የጋራ ኢኮኖሚ ልማትና አስተሳሰብ እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
“በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት አደረጃጀት ማስተካከል እና ዘርፉን የሚያንቀሳቅስ በቂ የሰው ሃይል በመመደብ መንግስት በትኩረት ሊሰራበት ይገባል” ብለዋል።
መንግስት ፓኬጅ አዘጋጅቶ ኢትዮጵያዊያን በዋና ዋና መዳረሻዎች ቅርሶች እንዲጎበኙ ማመቻቸት እንዳለበት ገልጸው፤ በዚህም ዜጎች እርስ በርስ እንዲተዋወቁ ማድረግ ለአገር አንድነት ጠቃሚ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሰጡበት እንደሚገባ ተናግረዋል።።
የትግራይ ምስራቃዊ ዞን አስጎብኚዎች ማህበር ተወካይ ወጣት ፍጹም ዘርኡ እንዳለው ዘርፉን ለማሳደግ ለአስጎብኚዎች ተከታታይ ስልጠና መስጠት ያሰፈልጋል።
“ለውጭ እና ለሀገር ውስጥ ዜጋ እኩል ክፍያ መጠየቅ ተገቢ አይደለም” ያለው ወጣቱ፤ “የሀገር ውስጥ የቱሪዝም እንቅስቃሴን ለማሳደግ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ሊሰራ ይገባል” ብሏል።