የህዝብ ብዛትና የምጣኔ ሃብት እድገትን አጣጥሞ መቀጠል እንደሚገባ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የህዝብ ብዛትና የምጣኔ ሃብት እድገትን አጣጥሞ መቀጠል እንደሚገባ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21/2013 ( ኢዜአ) የህዝብ ብዛትና የምጣኔ ሃብት እድገትን አጣጥሞ መቀጠል እንደሚገባ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን ገለጹ።
በአውሮፓዊያኑ 2050 ኢትዮጵያን ሊያጋጥሟት በሚችሉ ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች ዙሪያ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን የኢንተርኔት የቨርቿል ውይይት አድርገዋል።
ምሁራኑ በውይይታቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት የዛሬ 30 ዓመት 200 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ገምተዋል።
በመሆኑም የህዝቡን ቁጥር ማደግ ከኢኮኖሚ እድገት ጋር አሰናስሎ መቀጠል ይገባል ብለዋል።
የህዝቡን ቁጥር እድገት እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ለኢኮኖሚ ልማት ማዋል እንደሚገባም ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።
ግብርናን ማዘመን፣ ከተሞችን ማስፋፋትና መሰረተ ልማቶችን ማሟላት፣ አምራች ዘርፉን ማጠናከርና ኢንዱስትሪን ማስፋፋት ደግሞ ወሳኝ መፍትሄ መሆኑን አመላክተዋል።
ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ግን በአውሮፓዊያኑ 2050 የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥርና የኢኮኖሚ እድገቱ የማይመጣጠንና የችግር መንስኤ ይሆናል ብለዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ የምሁራኑ ምልከታ ወሳኝ ግብአት ይሆናል ብለዋል።
በውይይቱ ላይ በምሁራኑ የተነሱት ዋና ዋና ነጥቦችም ለመንግስት የፖሊሲ ግብአትነት ይጠቅማሉ ብለዋል።