ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ‘’አንድ ተማሪ ለአንድ ቤተሰብ’’ ፕሮጀክት ለማጠናከር መዘጋጀቱን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ‘’አንድ ተማሪ ለአንድ ቤተሰብ’’ ፕሮጀክት ለማጠናከር መዘጋጀቱን አስታወቀ
ጎንደር፣ ጥቅምት 21/2013 (ኢዜአ) ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባለፈው ዓመት ተግባራዊ ያደረገውን ‘’አንድ ተማሪ ለአንድ ቤተሰብ’’ ፕሮጀክት በተያዘው ዓመት ወደ ጽህፈት ቤት ደረጃ በማሳደግ አጠናክሮ ለመቀጠል መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡
የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የጀመረው የቤተሰብ ፕሮጀክት ኢትዮጵያዊ አንድነትን፣ አብሮነትንና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክር በመሆኑ እንደሚደግፉት ተናግረዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ለኢዜአ እንደገለጹት የቤተሰብ ፕሮጀክቱ ተቋሙ ከጎንደር ከተማ ህብረተሰብ ጋር በማስተሳሰር ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራው ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚመጡ አዲስ ተማሪዎች በከተማው ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በማገናኘት ትምህርታቸውን ጨርሰው እስኪመረቁ ድረስ እንደ ወላጅ እንዲከባከቧቸው የሚያስችል ነው።
ባለፈው ዓመት ከአንድ ሺህ በላይ የመጀመሪያ ዓመት አዲስ ተማሪዎች እያንዳቸው አንድ የቃል ኪዳን ቤተሰብ በከተማው ውስጥ እንዲመሰርቱ እንደተደረገም አውስተዋል፡፡
የቤተሰብ ፕሮጀክቱ ተማሪዎች የአካባቢውን ባህል፣ ልማድና ወግ እንዲሁም ማህበራዊ ህይወትን አውቀው በህይወት ዘመናቸው ትስስር ለመፍጠር እንደሚያስችል ዶክተር አስራት ተናግረዋል።
ተማሪዎቹን የተረከቡ የከተማው ነዋሪዎች እንደ ወላጅ ሃላፊነት በመውሰድ ሲንከባከቡዋቸው መቆየታቸውን ጠቅሰው በኮሮና ምክንያት ትምህርት ሲቋረጥ የአውሮፕላን ትኬት ጭምር ቆርጠው ወደ ቤተሰባቸው የሸኙ ምስጉን ወላጆች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
የብዝሃ ባህልና እሴቶችን ጠብቆ በማቆየት አብሮነትን ለማጠናከር የሚያስችለውን ፕሮጀክት ወደ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በማሳደግ በተያዘው ዓመት አጠናክሮ ለማስቀጠል መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ባለፈው ዓመት በፕሮጀክቱ የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገምና በማጥናት ያመጣውን ለውጥና ውጤት በማደራጀት በቀጣይ የሚጠናከርበትን አቅጣጫ አስቀምጦ የሚሰራ ነው።
የቤተሰብ ፕሮጀክቱን ፋይዳና ውጤት የተገነዘቡ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ልምዱን ለመቅሰም ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው ያሉት ዶክተር አስራት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም ተሞክሮውን ለማስፋት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
"የቤተሰብ ፕሮጀክቱ በከተማው ነዋሪዎች ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት ያገኘ ፕሮጀክት ነበር" ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ የሰላምና ልማት ሸንጎ አስተባባሪ አቶ ባዩህ በዛብህ ናቸው፡፡
ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት እየተሸረሸረ የመጣውን ኢትዮጵያዊ አንድነትንና አብሮነትን መልሶ ለማጠናከር የሚያግዝ በመሆኑ ሸንጎው ከዩኒቨርሲቲው ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑ ተናግረዋል፡፡
በግላቸውም ባለፈው ዓመት ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የመጣ የማህበራዊ ሳይንስ የመጀመሪያ ዓመት የዲግሪ ተማሪ እንደ ወላጅ ለመንከባከብ ፍቃደኛ በመሆን ፈርመው በመረከብ ቤተሰባዊ ግንኙነት እንደመሰረቱ ጠቅሰዋል፡፡
የጎንደር ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አንቺናአሉ ሞላ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ባደረገው ጥሪ እንደ ወላጅ ለመንከባከብ ፈቃደኛ በመሆን አንድ ተማሪ ፈርመው በመቀበል ባለፈው ዓመት የወላጅና የልጅ ግንኙነት መስርተው ጥሩ ጊዜ እንዳሳለፉ ገልጸዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በኮሮና ምክንያት የተቋረጠውን የትምህርት ስራ ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁንና በመጀመሪያው ዙርም 5 ሺ 400 ተማሪዎችን ለመቀበል መዘጋጀቱን ኢዜአ ቀደም ብሎ ዘግቧል።