ቀጥታ፡

ከቀጣዩ አገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ በፊት አገራዊ ሰላምና መረጋጋት ሊረጋገጥ ይገባል-ፓርቲዎች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21/2013 ( ኢዜአ) በዚህ ዓመት ከሚደረገው 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ በፊት ለአገራዊ ሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ የተራዘመው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ በተያዘው ዓመት እንዲካሄድ መወሰኑ አይዘነጋም።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫው ስለሚከናወኑ ተግባራት፣ የኮቪድ 19 ጥንቃቄዎችና በዝግጅቱ ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር አድርጓል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም እውነተኛና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ ከምርጫ በፊት መፈጸም ስለሚገባቸው አገራዊ ሁኔታዎች፣ ለፓርቲዎች መደረግ ስላለባቸው ትብብርናና በቦርዱ ዝግጅት ላይ ያተኮሩ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።

በአገሪቱ በተለያዩ ስፍራዎች የሚከሰቱ የዜጎች መፈናቀልና ግድያዎች፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝና ሌሎች አገራዊ ክስተቶች ከምርጫው በፊት እልባት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንደሆኑ አንስተዋል።

በዚህም ምርጫው አስፈላጊ ቢሆንም ከምርጫ በፊት መፈጸም ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ለአብነትም በኢትዮጵያ አሁናዊ አገራዊ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ምርጫ ለማካሄድ አገራዊ ሰላምና መረጋጋት መቅደም እንዳለበት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ ምርጫው በተያዘለት ጊዜ እንዲካሄድ ፓርቲያቸው እንደሚሻ ገልጸው፤ የሰላም ጉዳይ ግን ሁሉም ወገኖች ትኩረት ሊሰጡት ይገባል ይላሉ።

ለዚህ ደግሞ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጥንቃቄ እርምጃዎች ባሻገር፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሰላምና ጸጥታ ጉዳይ መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረ በበኩላቸው ወደ ምርጫ ከመገባቱ በፊት ፓርቲዎች ተንቀሳቅሰው ሃሳባቸውን ለመሸጥ አስቻይ ሁኔታ እንደሌላቸው ይገልጻሉ።

በርካቶቹ በተፈናቀሉበት፣ የክልልነት ጥያቄ ያነሱ አካባቢዎች በበረከቱበት ምርጫ በምን ሁኔታ ይፈጸማል የሚሉት ጉዳዮች እንደሚያሳስቧቸው አቶ ማሙሸት ይናገራሉ።

ፓርቲዎቹ የምርጫውን መካሄድ ቢደግፉም የዜጎችና የአገር ደህንነት ግን እንደሚያሳስባቸው ይገልጻሉ።  

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ፓርቲዎች የምርጫ ቅድመ ሁኔታዎች እልባት እንዲያገኙ መጠየቃቸው ተገቢ ሃሳብ እንደሆነ ይገልጻሉ።

ቦርድ አስፈጻሚ አካል በመሆኑ ሁሉንም ጉዳዮች ለአብነትም ብሄራዊ መግባባት ላይ ኃላፊነት እንደሌለው ይናገራሉ፤ በሕግ ኃላፊነት በተሰጠው ጉዳዮች ግን እልባት እንዲያገኙ እንደሚሰራ ይገልጻሉ።

ከምርጫ ሂደት ጋር የተያያዙ የምርጫ ፀጥታ ችግሮች እንዳይከሰቱ ግን ቦርዱ እየሰራ መሆኑን ሰብሳቢዋ አመልክተው፤ ለዚህም ችግሮችን ቀድሞ ለመከላከል የመረጃ ቋት እንደሚዘረጋ ተናግረዋል።

ኮቪድ 19 ወረርሸኝም ሆነ ሌሎች የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮችም ጎን ለጐን በማቃለል ምርጫው በተያዘለት ጊዜ መፈጸም እንደሚቻልም አብራርተዋል።

ለዚህ ደግሞ የኮቪድ 19ንም ሆነ በሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች በተመለከተ የሰላምና ጸጥታ፣የሲቪክ ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትን በማሳተፍ በሚዋቀረው አስተባባሪ ኮሚቴ በኩል እንደሚሰራ ወይዘሪት ብርቱካን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም