በእንባ ጠባቂና ግልግል ዳኝነት ጉዳያቸው የሚታይላቸው ተቋማት የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤቱ አባላት ብቻ ይሆናሉ - ኢዜአ አማርኛ
በእንባ ጠባቂና ግልግል ዳኝነት ጉዳያቸው የሚታይላቸው ተቋማት የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤቱ አባላት ብቻ ይሆናሉ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21/2013 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የእንባ ጠባቂና የግልግል ዳኝነት ጉዳያቸው የሚታይላቸው ተቋማት የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤቱ አባል የሆኑ ብቻ መሆናቸው ተገለጸ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በሥሩ ያዋቀራቸውን የእንባ ጠባቂና የግልግል ዳኝነት አባላት ለምክር ቤቱ አስተዋውቋል።
ምክር ቤቱ የተቋቋመው በ2008 ዓ.ም ቢሆንም ወደ ሥራ የገባው ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እንደሆነ ይታወቃል።
ይኸው ምክር ቤት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ጋዜጠኞች በሥራቸው ላይ የሚደርስባቸውን በደልና አቤቱታ በመቀበል ጉዳዩን ተመልክቶ ውሳኔ የሚሰጥም ነው።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ እንደገለጹት እስካሁን 46 የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት አባላት ሲኖሩ ሌሎች ያመለከቱም አሉ።
የምክር ቤቱ አባል መሆን የሚችሉ ህጋዊ ፈቃድ ያላቸው የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እንጂ ግለሰቦች አለመሆናቸውንም አብራርተዋል።
የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ህጋዊ ፈቃድ ያላቸው ከመሆን ባለፈ የምክር ቤቱን የስነ-ምግባር ደንብና መመሪያ ተቀብለው የፈረሙ መሆን እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የእንባ ጠባቂና የግልግል ዳኝነት አባላት አስመራጭ ኮሚቴ አቶ አብዱ አሊ ሒጅራ በበኩላቸው በምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ጉዳዮችን የሚያየው በምክር ቤቱ አባላት አቤቱታ ሲቀርብ ብቻ መሆኑን አብራርተዋል።
በተለያዩ ሃገራት ጉዳዮችን በራሳቸው ምርመራ አድርገው የሚመለከቱ መሆናቸውን ገልጸው በኢትዮጵያ ግን ቅሬታ የቀረበ እንደሆነ ነው ለጊዜውም ቢሆን ጉዳዩ የሚታየው ብለዋል።
መተዳደሪያ ደንቡ ተፈጻሚ የሚሆነው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት አባል በሆኑ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ላይ ብቻ መሆኑንም አስረድተዋል።
ሌላኛው የአስመራጭ ኮሚቴ አርቲስት አበበ ባልቻ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት አባል የሆነ ማንኛውም የመገናኛ ብዙኃን ተቋም በመተዳደሪያ ደንቦቹ ተገዥ መሆን እንዳለበት ገልጿል።
ነገር ግን በምክር ቤቱ የእንባ ጠባቂና የግልግል ዳኝነት ውሳኔ ቅር የተሰኘ አካል ካለ ወደ መደበኛው ፍርድ ቤት የመሄድ ሙሉ መብት እንዳለው መዘንጋት የለበትም ብሏል።
ምክር ቤቱ የእንባ ጠባቂ እንዲሁም የግልግል ዳኝነት አባላት አቤቱታ በመቀበል ውሳኔ የሚሰጥ በመሆኑ፣ የአፈጻጸም ደንብና መመሪያ የማውጣት ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል አቶ አብዲ አሊ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ዓላማው ክፉና ደጉን ለይቶ በህሊና የሚተዳደር ሥርዓት መገንባት መሆኑን ገልጸው ከዚህ እሴት ውጭ የሚሆኑ አካላትን ህዝቡ "ሃይ" ሊላቸው ይገባል ብለዋል።
መገናኛ ብዙኃን ህግና መመሪያዎችን በማክበር የህግ ተገዥ መሆናቸውን በተግባር ማሳየት አለባቸውም ብለዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ከመንግሥት ጣልቃ ገብነትና ተፅዕኖ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ መሥራት የሚያስችል አደረጃጀት ያለው መሆኑንም አቶ አማረ ተናግረዋል።