ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በህዳሴ ግድብ ላይ የሰጡትን አስተያየት በመቃወም በበይነ መረብ ፊርማ ማሰባሰብ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በህዳሴ ግድብ ላይ የሰጡትን አስተያየት በመቃወም በበይነ መረብ ፊርማ ማሰባሰብ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21/2013 ( ኢዜአ) የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሰጡትን አስተያየት በመቃወም በበይነ መረብ ፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ በይፋ ተጀመረ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ፣ በግድቡ ዙሪያ ሙግቶችን የሚያደርገው መሀመድ አል-አሩሲን ጨምሮ አርቲስቶችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ነው የፊርማ መሰባሰብ ዘመቻው የተጀመረው።
የጽህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም እንደተናገሩት፤ የፊርማ ማሰባሰቡ "ፊርማችን ለግድባችን" በሚል መሪ ሃሳብ የሚከናወን ነው።
“የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻው ዓላማ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያደረጉት ተገቢ ያልሆነ ንግግር በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰ መሆኑን ለማሳወቅ ነው” ብለዋል።
በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥም 100 ሺህ ፈርማ ለማሰባሰብ መታቀዱን ገልጸዋል።
በመሆኑም White house petition እና change.org petition በተሰኙ ድረ ገጾች ገብቶ መፈረም እንደሚቻል ጠቁመዋል።
በተለይም በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ሰልፍ ከማድረግ ጀምሮ በግል ጥረታቸው ፊርማ ማሰባሰብ እንደጀመሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
አሁን ግን በተደራጀና ወጥ በመሆነ መልኩ ፊርማ ማሰባሰብ አስፈላጊ በመሆኑ ይህ ዓለም አቀፍ የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ መጀመሩን ተናግረዋል።
"የፕሬዝዳንቱ ንግግር የአሜሪካዊያን አቋም ነው ብለን አንወስድም'' ያሉት አቶ ኃይሉ፤ በቀጣናው ሠላም ለማስፈን ጥረት ከሚያደርግ አካል እንዲህ አይነት ንግግር መሰማቱም ሃላፊነት የጎደለው ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያዊያን የሚሰጡት ድጋፍ የበለጠ መጠናከሩን ጠቅሰው ግድቡ ውኃ ከያዘ በኋላ በሃምሌ ውስጥ 119 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር እንደተሰበሰበ አመልክተዋል።
በአዲስ አበባም የድጋፍ የማሰባሰቡ ሂደት በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የፊርማ ዘመቻው አስተባባሪ አቶ ፍሬው በቀለ በበኩላቸው “ፊርማው ለህዝብ ክፍት እንዲሆን በቅድሚያ 150 ሰዎች መፈረም እንዳለባቸው ጠቁመው ፊርማው 100 ሺህ ሲደርስ ደግሞ የአሜሪካ መንግስት መልስ የሚሰጥ የሆናል” ብለዋል።
ፊርማው ለአሜሪካ መንግስት ብቻም ሳይሆን ለአፍሪካ ኀብረት፣ የአውሮፓ ህበርትና ሌሎችም ዓላም አቀፍ ተቋማት ገቢ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።